Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል 81 የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በ13 ቢሊየን ብር እየተገነቡ መሆኑን አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልሉን ግብርና ከዝናብ ጥገኝነት የሚያላቅቁ 81 አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በ13 ቢሊየን ብር እየተገነቡ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ።
የአየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው ድርቅ በክልሉ በእንስሳት ሀብትና በሰብል ልማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ጠቁመው÷ በተለይ በቦረና፣ ምስራቅና ምዕራብ ጉጂ፣ ምስራቅ ባሌና ባሌ ዞን፣ ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ የተከሰተው ድርቅ አሁንም ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።
ይህን ችግር መቋቋም የምንችለው የተፈጥሮ ዝናብ በመጠበቅ ሳይሆን አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ልማት ግድቦችን በስፋት በመገንባት በበጋው ጭምር ሰብልና የእንስሳት መኖን በብዛት ማምረት ስንችል ነው ያሉት አቶ ሽመልስ÷ ለዚህም የክልሉ መንግሥት በ13 ቢሊየን ብር ወጪ 81 አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ፕሮጄክቶች እየገነባ ነው ብለዋል፡፡
ይህም ድርቁ እያስከተለ ያለውን ተፅዕኖ ከመቋቋም ባለፈ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ አርብቶ አደሩን ማህበረሰብ በዘላቂነት ከተረጂነት ለማላቀቅ ያስችላል ብለዋል።
እንዲሁም በክልሉ ቆላማ አካባቢዎች ያሉ ለም መሬቶችን ወደ ልማት ለማስገባት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ አርብቶ አደሩ በብቸኝነት ከያዘው የእንስሳት ሀብት ልማት በተጨማሪ ወደ ከፊል አርሶ አደር ለማሻገር ግብ በማስቀመጥ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
የክልሉ መንግሥት በቀጣይ አራት ዓመታት ከ250 በላይ አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት አቅዶ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ይህም የክልሉን ግብርና ከተፈጥሮ የዝናብ ጥገኝነት ከማላቀቅ ባለፈ በሁሉም ዞኖች በበጋ ወቅት ከስንዴ በተጨማሪ ሌሎች ዋና ዋና ሰብሎችና የእንስሳት መኖን ለማልማት ጭምር ነው ብለዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.