Fana: At a Speed of Life!

የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ በተቀናጀ አግባብ የመረጃ ፍሰትና ስርጭትን ማከናወን ይጠበቅበታል – ዶክተር ለገሰ ቱሉ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች ለመሻገር በምታደርገው ጥረት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ የተቀናጀና መዋቅራዊ ሂደቱን በጠበቀ አግባብ የመረጃ ፍሰትና ስርጭትን መከወን እንዳለበት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ አሳሰቡ።

የፌዴራልና የክልል የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ዓመታዊ ጉባዔ በአዳማ እየተካሄደ ነው።

በጉባኤው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ፍትሕና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ዕፀገነት መንግስቱ እና የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ታድመዋል።

ለሁለት ቀናት የሚቆየው ጉባዔው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት እንዲሁም የክልልና የፌዴራል ተቋማት የ2014 የስራ አፈፃፀም ክንውን እና የ2015 በጀት ዓመት የስራ ዕቅድ ለውይይት እንደሚቀርብ ተገልጿል።
በዛሬው መርሐ ግብርም በቀጣይ 5 ዓመታት ገቢራዊ የሚደረገው የአምስት ዓመት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ስትራቴጂክ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ውስጣዊና ውጫዊ መልከ ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁማ በኢኮኖሚው መስክ በስኬት መሻገሯን የሕዳሴ ግድብን፣ አረንጓዴ አሻራ፣ በበጋ ስንዴ ምርትና ሌሎች አገራዊ ፕሮጀክቶች ስኬትን ለአብነት አንስተዋል።

የኮሙኒኬሽን አገልግሎት በአዲስ አደረጃጀት ዘግይቶ የተቋቋመና የራሱ ውስንነቶች ቢኖሩትም ባለፉት 10 ወራት የመንግስትን መረጃ ለህብረተሰቡ በማድረስ ረገድ በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ የተሻለ ስራዎች ስለመከናወናቸው አንስተዋል።

የኮሙኒኬሽን መዋቅሩ በመረጃ ስርጭት ረገድ በተናበበና በተቀናጀ አግባብ መረጃዎችን መጋራት ላይ መስራቱን አውስተዋል።

ኢትዮጵያ የገጠማትን ችግር በሰላም ለመቋጨት መንግስት የሰላም እጅ ቢዘረጋም፥ ባንዳዎችና ፀረ-ሰላም ኃይሎች የሰላም ጥሪውን እያደናቀፉ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

አገራዊ የሰላም ችግሩን በሰላም ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ትክክለኛና ወቅትዊ መረጃዎችን በማቅረብ ከፍተኛ ኃላፊነት እንደሚጠበቅበት ነው ሚኒስትሩ ያስገነዘቡት።

የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ በተናበበ፣ ወጥነትና ብዝሀነትን በጠበቀ፣ በተቀናጀና መዋቅራዊ ሂደቱን በጠበቀ አግባብ የመረጃ ፍሰት እንደሚያስፈልግ ገልፀው፥ ለዚህም የጋራ አገራዊ አጀንዳዎች ያሉት የኮሙኒኬሽን ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ ይጠይቃል ነው ያሉት።

ዘርፉ የሚጠበቅበትን አገራዊ ሚና እንዲወጣም የ5 ዓመት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

የዕቅዱ ዓላማም መረጃን በተማከለ፣ በፍጥነትና በጥራት ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ ማስቻል መሆኑን አስረድተዋል።
የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ዕቅዶች እንደ አገሪቱ ሁናቴ ተለዋዋጭነት ስላለው በየወቅቱ እየተከለሰ እንደሚቃኝም ነው ያስረዱት።

የፌዴራልና የክልል የዘርፉ ተቋማትም ለዕቅዱ ስኬትና የሚጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ በጋራ መምከርና መወሰን እንደሚጠበቅባቸው ማሳሰባቸውንና መሰል ጉባዔዎች በቀጣይ እንደሚካሄዱ ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.