በክልሉ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል – አቶ ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሉ በትምህርት ተደራሽነት የተገኘውን ውጤት በትምህርት ጥራትም መድገም ያስፈልጋል ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዐሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ፡፡
በሐረሪ ክልል የ2015 የትምህርት ዘመን የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ የንቅናቄ መድረክ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪና ሌሎች የክልልና የወረዳ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድሩ እንደተናገሩት ፥ ትምህርት ቤቶች ትውልዱ በእውቀትና በስነምግባር ታንፆ የሚወጣበት ወሳኝ ስፍራ ነው።
በመሆኑም በክልሉ በትምህርት ተደራሽነት የተገኘውን ውጤት በትምህርት ጥራትም መድገም እንደሚያስፈልግ ጠቁመው በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲቀረፉም በተለይ አመራሩ፣ መምህራን እና ወላጆች ሚናቸውን ማጎልበት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱጀባር መሀመድ በበኩላቸው ፥ ሁሉም የወረዳ አመራሮች በትምህርት ቤት ደረጃ የተዘጋጁ እቅዶችን መፈተሽ እና ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ የ2015 የትምህርት ዘመን ዝግጁነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።
ወረዳዎች የትምህርት አመራሮችና መምህራንን በመፈተሽ ለውጤት ማጣት ምክንያት በሆኑት ላይ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ይገባል ሲሉም ነው የገለጹት።
በ2014 በጀት ዓመት በትምህርት ዘርፉ አበረታች ተግባራት የተከናወኑ ቢሆንም የትምህርት ጥራት ችግር ይስተዋላል ያሉት ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ ናቸው።
በ2015 በጀት ዓመት የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል፣ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሳደግና የግብዓት ችግርን ለመቅረፍ ማህብረሰቡንና የሚመለከታቸው አካላትን ባሳተፈ መልኩ ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የ2015 የትምህርት ዘመን ከወዲሁ የተማሪዎች ምዝገባ፣ በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ትግበራና ቀጣይ ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ሀገራዊ ፈተና ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነ ማንሳታቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።