Fana: At a Speed of Life!

የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመጨረሻ ውጤት ይፋ መሆንን ምክንያት በማድረግ ከብልፅግና ፓርቲ የቀረበ የምስጋና መልዕክት፤

እጅግ የተከበራችሁ ውድ ኢትዮጵያዊያን፣

የተከበራችሁ የፖለቲካ ማኅበረሰብ አባላትና የምርጫው ባለድርሻ አካላት፤

ዛሬ ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲን በተግባር ያሳዩበት፣ ታሪካቸውን በደማቁ የጻፉበት እና አፍሪካ ስለ ራሷ በራሷ መወሰን እንደምትችል ለአለም ያበሰሩበት ታላቅ ምዕራፍ መመዝገቡ ይፋ ተደርጓል!

በታሪካዊው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ፣ ሕዝባችን ትናንትን በማከም እና ነገን በፅኑ መሠረት ላይ በመተለም፣ የኢትዮጵያን ከፍታ እውን ለማድረግ ፋና ወጊ ለሆነው ለብልፅግና ፓርቲ ዳግም ታላቅ ኃላፊነትና አደራ ሰጥቷል። ብልፅግና ፓርቲ ይህንን ታላቅ ሕዝባዊ አደራ የተቀበለው በስኬቱ ሳይኩራራ፣ ጉድለቶቹን እያረመ ሕዝብን በቅንነት ለማገልገልና ቃልን በተግባር ለማረጋገጥ ባለው ፅኑ እምነት ነው። ለዚህ ታላቅ ክብር መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰጠንን የዴሞክራሲ ውል በታላቅ ትሕትና እና በከፍተኛ አክብሮት እንቀበላለን።

ይህ የምስጋና መልዕክት እኛን ለመረጡን ዜጎች ብቻ የቀረበ አይደለም፤ ይልቁንም ያሻቸውን አማራጭ በመምረጥ መብታቸውን የተጠቀሙ፣ በካርዳቸው ድምፅ በመንፈግም ቢሆን ሂደቱ ሕጋዊና ሰላማዊ እንዲሆን የበኩላቸውን የተወጡ ዜጎችን ሁሉ ያጠቃልላል። ምክንያቱም የእያንዳንዱ ዜጋ ተሳትፎ የሀገራችን ዴሞክራሲ እውነተኛ አሸናፊ እንዲሆን አድርጓል።

በዚህ ምርጫ ሂደት ውስጥ በግልጽ መለየት ያለበት መሠረታዊ እውነት አለ፡- የብልፅግና ፓርቲ አብላጫ ድምፅ አግኝቶ መንግሥት የመመሥረት መብት ማግኘቱ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና የማረጋገጥ ራዕይ ሰንቆ ውጤታማ ጉዞ እያደረገ እንዳለ ፓርቲ እንደ ትልቅ እድል የሚወሰድ ሲሆን፤ የምርጫው ፍጹም ሰላማዊ፣ ነጻ፣ ፍትሓዊና ተዓማኒ ሆኖ መጠናቀቅ ግን የውድ ሀገራችን ኢትዮጵያ እና የመላው ሕዝቧ ስትራቴጂያዊ አሸናፊነት ማረጋገጫ ነው!

ይህ ምርጫ እንደ ከዚህ ቀደሙ የተለመደ የፖለቲካ ውድድር ወይም ወቅታዊ ኩነት አልነበረም። ይህ ምርጫ የውስጥና የውጭ የሴራ መረቦችን የበጣጠሰ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በተግባር ያደመቀ፣ የዴሞክራሲ ተቋሞቻችንን ብስለት ያጎለበተ ታላቅ የታሪክ እመርታ ነው። ኢትዮጵያ በማንኛውም ውጫዊ ጫና ሳትበገር፣ ሙሉ በሙሉ በራሷ ሁለንተናዊ አቅም ያከናወነችው ይህ ታሪካዊ ክንውን ሀገር በቀል ዴሞክራሲን እና አህጉራዊ ሉዓላዊነትን ያረጋገጠ በመሆኑ ለመላው አፍሪካ ኩራትና ተምሳሌት ሆኗል።

ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መሳተፋቸው የሕዝባችንን የፖለቲካ ንቃት የሚያሳይ ሲሆን፣ የሕዝብን ድምፅና ሉዓላዊ ፈቃድ ማክበር የመንግሥትና የማንኛውም የፖለቲካ ተዋናይ ቀዳሚ ተግባር መሆኑ በተግባር ተረጋግጧል። በምርጫው የኢትዮጵያ ጠላቶች ሀገርን ለማወክ የሸረቡት ተንኮልና መፍጨርጨር በሕዝባችን ብስለት ሙሉ በሙሉ እንዲመክን ተደርጓል።

የዚህ ታሪካዊ ስኬትና የኢትዮጵያ አሸናፊነት መረጋገጥ ያለ ባለድርሻ አካላት ተጋድሎ ሊታሰብ አይችልም። በመሆኑም ፓርቲያችን ብልፅግና ለምርጫው ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት በሙሉ የላቀ ምስጋናውንና አክብሮቱን ያቀርባል፡፡

በተለይም የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገር ህልውናንና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባት ያለውን የማይናወጥ ወገንተኝነት በተግባር ባሳየበት በዚህ ታሪካዊ የምርጫ ሂደት፣ በተለይም በምርጫው ዕለት ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ እግር ጥሎት ሳይሆን ራዕይ መርቶት፣ ብርድና ድካምን በሀገራዊ ፍቅር እያሸነፈ፣ እስከ ሚቀጥለው ቀን ሌሊት 10 ሰዓት ድረስ ለሙሉ 24 ሰዓታት ያለመሰልቸት በታላቅ ትዕግሥትና ዲሲፕሊን ተሰልፎ ሕገ-መንግሥታዊ መብቱን ለመጠቀም ያሳየው ታሪካዊ ቁርጠኝነትና የፖለቲካ ብስለት ለፓርቲያችን ብልፅግና ብቻ ሳይሆን ለመላው ታዳጊ ዴሞክራሲዎችና ለአፍሪካ አህጉር አዲስ የተግባር ማስተማሪያና የሉዓላዊነት ተምሳሌት በመሆኑ፣ ለዚህ አስተዋይና ስልጡን ሕዝብ ፓርቲያችን ከፍ ያለ አክብሮቱን፣ ኩራቱንና ጥልቅ የሆነ ሕዝባዊ ምስጋናውን በታላቅ ትሕትና ያቀርባል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱን ፍፁም በሆነ ገለልተኝነት፣ በከፍተኛ ሙያዊ ብቃት፣ በትዕግስትና በሕጋዊነት መርህ በመምራት የኢትዮጵያን ተቋማዊ ነጻነት በዓለም ፊት ስላስመሰከረ የላቀ አድናቆትና ምስጋና ይገባዋል።

42 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከ10 ሺህ በላይ ዕጩ ተወዳዳሪዎች በሂደቱ መሳተፋቸው ሕዝባችን አማራጮችን በሰፊው መዝኖ እንዲመርጥ አድርጓል። በመሆኑም ከውጭና ከውስጥ ይነፍስ የነበረውን የሀሰት ወጀብ ተቋቁማችሁ፣ ለሰላማዊ የሃሳብ ውድድር እና ለሕግ የበላይነት ያሳያችሁት ስልጡን ቁርጠኝነት ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ባህል ማበብ ታላቅ መሠረት ጥሏል። እናንተ የሕዝብ ሉዓላዊነት አክባሪዎችና የሀሳብ ፖለቲካ ታጋዮች ናችሁና ትልቅ ክብርና ምስጋና ይገባችኃል።

የፌዴራልና የክልል የጸጥታና ደህንነት ተቋማት፣ ሕዝቡ ያለምንም ስጋት በነጻነት ወጥቶ ድምፁን መስጠት እንዲችል ሌት ተቀን በመሥራት፣ መስዋዕትነት በመክፈል እና ሀገርን ከጥፋት ኃይሎች በጽናት በመጠበቅ ታላቅ ኃላፊነት ተወጥተዋል። እናንተ የሀገር ጠበቃ እና የሕዝብ የቁርጥ ቀን ልጆች ናችሁና ትልቅ ክብርና ምስጋና ይገባችኃል።

የሚዲያ ተቋማት ሕዝቡ በመብቱ እንዲጠቀም፣ ነፃና ሚዛናዊ የምርጫ ድባብ እንዲፈጠር ከቅድመ ምርጫ እስከ ድህረ ምርጫ ሙያችሁን አክብራችሁና ለሀገራችሁ በፅኑ ታምናችሁ ላበረከታችሁት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ምስጋና ይገባችኋል።

የሀገር ውስጥ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ በመንቀሳቀስ፣ ለዜጎች ሰፊ የዴሞክራሲና የመራጮች ትምህርት በመስጠት፣ የሕዝባችን የፖለቲካ ንቃት እንዲያድግና መብቱን እንዲረዳ በማድረግ ረገድ የማይተካ ሚና ተጫውታችኋል። በምርጫው ዕለትም በሺዎች የሚቆጠሩ ታዛቢዎችን በየምርጫ ጣቢያው በማሰማራት ሂደቱ ፍጹም ሰላማዊ፣ ሕጋዊና ፍትሐዊ እንዲሆን ሀገር በቀል አቅማችሁንና ተቋማዊ ነጻነታችሁን በተግባር ስላሳያችሁ ታላቅ አክብሮትና ምስጋና ይገባችኋል።

የአፍሪካ ህብረት እና ኢጋድ “ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ” የሚለውን ታላቅ መርህ በተግባር በማሳየት፣ አህጉራዊና ቀጠናዊ ተቋማቶቻችን ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት እንደሚችሉ ዳግም አስመስክረዋል። የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የአህጉራችን ኩራትና የተምሳሌትነት ማሳያ መሆኑን በመመስከር፣ የምርጫውን እውነተኛነትና ተዓማኒነት በዓለም መድረክ ከፍ ስላደረጋችሁ፤ ላሳያችሁት ፅኑ ፓን-አፍሪካዊ ወንድማማችነት፣ ቀጠናዊ አጋርነትና ታሪካዊ ቁርጠኝነት ፓርቲያችን ብልፅግና የላቀ ምስጋናውንና አክብሮቱን ያቀርባል።

ሌሎች ቀጣናዊ ተቋማትና ወዳጅ ሀገራትም የኢትዮጵያን ተጨባጭ እውነታ በትክክል በመረዳት፣ አጠቃላይ የምርጫውን ሂደት በልዩ ትኩረት ለተከታተላችሁ እና ሂደቱ ፍጹም ሰላማዊ፣ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ መጠናቀቁን በመመስከር አዎንታዊና ጠቃሚ ግብረ መልሶችን ለሰጣችሁ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አባላት፣ ቀጣናዊ ተቋማትና ወዳጅ ሀገራት በሙሉ ፓርቲያችን ብልፅግና የላቀ ምስጋናውን ያቀርባል።

የእናንተ ሚዛናዊና እውነተኛ ምስክርነት የሀገራችንን ተቋማዊ ተዓማኒነት የሚያጎለብት ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ጀመረችውን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ የሚደግፍ ታሪካዊና ስትራቴጂያዊ አጋርነት ማረጋገጫ በመሆኑ በታላቅ አክብሮት እንቀበለዋለን።

ብልፅግና ፓርቲ በሕዝብ የተሰጠውን አዲስ የዴሞክራሲና ማኀበራዊ ውል መሠረት በማድረግ፣ የሥልጣን ባለቤትነቱ የሕዝብ መሆኑን በተግባር ያረጋግጣል። በቀጣይ ዓመታት መንግሥታችን የሕዝባችንን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ዘርፈ ብዙ ውጤታማ ሥራዎች አጠናክሮና አስፍቶ የሚሄድ ሲሆን፣ በተለይም የሕዝብ ጥያቄዎች የሆኑና የጋራ ጥረት በሚጠይቁ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ከሕዝባችንና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በሙሉ በመተባበር ምላሽ እንዲያገኙ ርብርብ የምናደርግ ይሆናል።

ከዚህ አንፃር ዘላቂ ሰላምና ፀጥታን ለማስፈንና የሕግ የበላይነትን በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባት፣ የኑሮ ውድነትን ለማቃለልና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ዘላቂ የሥራ ዕድሎችን በስፋት ለመፍጠርና የዜጎቻችንን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ሀገራዊ አስተዋጽኦ ለማሳደግ፣ የተጀመረውን የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን በሀገር አቀፍ ደረጃ በስፋት በማስፋፋት፣ የቢሮክራሲ ማነቆዎችን በመበጣጠስና የአገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ በማዘመን፣ ሌብነትንና ብልሹ አሠራርን በቆራጥነት ለመከላከልና የተገልጋዩን ሕዝብ እርካታ በከፍተኛ ደረጃ ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት የምንሰራ ይሆናል።

በተጨማሪም በመገባደድ ላይ የሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ሂደት የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ በሚገባ በመደገፍ፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን ይበልጥ ነፃ፣ ገለልተኛና ጠንካራ እንዲሆኑ በማጠናከር፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ብሔራዊ ጥቅማችንን ማዕከል ባደረገ መልኩ በትብብር በመስራት ገንቢ ሃሳቦቻቸውንና አቅማቸውን ለማካተት የጀመርናቸውን ጥረቶች የምናልቅ ይሆናል።

በአጠቃላይ ብልፅግና ፓርቲ የገባውን ቃል ሳይሸራረፍ በመተግበር፣ ምርጫ የሥልጣን መቆናጠጫ ሳይሆን ሕዝብን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገያ ታላቅ አደራ መሆኑን በተጨባጭ ያረጋግጣል። ለዚህም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና በተግባር የማረጋገጥ ታሪካዊ ጉዟችንን ከምንጊዜውም በላይ በበለጠ ትጋት፣ አንድነትና ቁርጠኝነት አጠናክረን ለመቀጠል ለተከበረው ሕዝባችን ዳግም ቃላችንን እናድሳለን!

ብልፅግና ፓርቲ

ሰኔ 14 ቀን 2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.