በአዲሱ ዓመት የህወሓትን ወረራ በመቀልበስ የሕዝቡን ውስጣዊ አንድነት እናስጠብቃለን – ር/መስተዳድር ይልቃል ከፋለ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2015 አዲስ ዓመት የተጋረጠብንን የአሻባሪው ህወሓት ወረራ በመቀልበስ የሕዝባችንን ውስጣዊ አንድነት እናስጠብቃለን ሲሉ አማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ባለፈው ዓመት አሸባሪው ህወሓት ሰላም ወዳዱ የአማራ ክልል ሕዝብ ላይ ወረራ በመፈጸም በዜጎች ላይ ሰቆቃ፣ የዘር ፍጅት፣ መፈናቀል፣ የሃብት ውድመት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማድረሱን አስታውሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ ታጋሹና ጀግናው የክልሉ ሕዝብ ከጸጥታ ኃይሎች እና ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ አኩሪ ገድል ፈጽሟል ነው ያሉት፡፡
በ2014 በጀት ዓመት ለመልሶ ግንባታና ለልማት ሥራዎች ትኩረት በመስጠት ጦርነቱ ጫና ያሳደረበትን ኢኮኖሚ ለመቋቋም ውጤታማ ሥራዎች የተከናወኑበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአሸባሪው ህወሓት የተፈናቀለውን የክልሉ ሕዝብ መልሶ ለማቋቋምና የወደሙ ሃብቶችን ለመገንባት መላው የክልሉ ሕዝብና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ላሳየው ርብርብም ምስጋና አቅርበዋል።
ሁለተኛው ዙር ወረራ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ጀግንነት ከተቀለበሰ በኋላ የመልሶ ግንባታና የልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት መደረጉንም አንስተዋል፡፡
በዚህም በበጋ ስንዴ ልማት፣ በክረምት ግብርና በዘር የተሸፈነ መሬት ውጤታማነት፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እጥረትን ለመፍታት የተደረገው ንቅናቄ፣ የአረንጓዴ ልማት ሥራ እና የኢንቨስትመንት እድገት አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያን ሰላም በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ብሔራዊ የሰላም የውይይት የአማራ ክልል ሕዝብና መንግሥት ጽኑ እምነት እንዳለው አውስተው÷ በአንጻሩ ለሰላም አማራጭ በሩ የማይከፈተው አሸባሪው ህወሓት በተደጋጋሚ ወረራ እየፈጸመ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡
ለደቂቃም ቢሆን አሸባሪው ህወሓትንና የትግራይን ሕዝብ አንድ አድርገን አንመለከትም ያሉ ት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷ መንግሥት የትግራይና የአማራ ሕዝብ ወንድማማችነት በአሸባሪው ቡድን የጠላትነት እንቅስቃሴ እንዳይገታ አበክሮ እንደሚሠራም ተናግረዋል።
የክልሉ ሕዝብ ለሰላም ዝግጁ የመሆኑን ያክል ክብርና ማንነቱን ለማስጠበቅ የኢትዮጵያ አንድነት ጠላት የሆነውን ቡድን ለመደምሰስ፥ ከጥምር ሃይሉ ጎን ተሰልፎ ባሳየውና እያሳየ ባለው አኩሪ ደጀንነቱ ሊመሰገን ይገባዋል ብለዋል።
የኑሮ ውድነቱን ፍትሃዊ የገበያ ሥርዓት በማስፈንና የተጀመረውን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ እድገት ማሻሻያ በስኬት በመተግበር ለመላው ሕዝብ የድል፣ የሰላምና የልማት ዓመት እንደሚሆን ያላቸውን እምነት መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!