Fana: At a Speed of Life!

ብራዚል ከጃፓን – ጀርመን ከፓራጓይ – ኔዘርላንድስ ከሞሮኮ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ እየተካሄደ በሚገኘው የ2026 የዓለም ዋንጫ የ32ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ዛሬ ሦስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡

በጥሎ ማለፉ ብራዚል ከጃፓን ምሽት 2 ሰዓት፣ ጀርመን ከፓራጓይ ምሽት 5 ሰዓት ከ30 እንዲሁም ኔዘርላንድስ ከሞሮኮ ሌሊት 10 ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡

የአምስት ጊዜ የመድረኩ አሸናፊ ብራዚል ሰባት ነጥብ በመሰብሰብ ምድብ ሦስትን በበላይነት በማጠናቀቅ ጥሎ ማለፉን የተቀላቀለች ሲሆን፥ ጃፓን በአንጻሩ በምድቧ ምንም ሽንፈት ሳታስተናግድ 2ኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡

ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በ2006ቱ የዓለም ዋንጫ የምድብ መርሐ ግብር ያደረጉትን ጨዋታ ብራዚል 4 ለ 1 ማሸነፏ አይዘነጋም፡፡

የብራዚል እና ጃፓን አሸናፊ በ16ቱ ጥሎ ማለፍ ከኮትዲቯር እና ኖርዌይ አሸናፊ ጋር የሚገናኝ ይሆናል፡፡

በሌላ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ምድብ አምስትን በበላይነት ያጠናቀቀችው ጀርመን ምርጥ ሦስተኛ በመሆን 32ቱን ከተቀላቀለችው ፓራጓይ ጋር ትጫወታለች፡፡

ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በ2002ቱ የዓለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ ላይ የተገናኙ ሲሆን፥ ጀርመን ጨዋታውን በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፍ ችላ ነበር፡፡

የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች አሸናፊ ሩብ ፍጻሜውን ለመቀላቀል ከፈረንሳይ እና ስዊድን አሸናፊ ጋር ይፋለማል፡፡

በሌላ የዛሬ መርሐ ግብር ከምድብ-ሦስት 2ኛ ደረጃን በመያዝ 32ቱን የተቀላቀለችው ሞሮኮ ከምድብ ስድስት አሸናፊዋ ኔዘርላንድስ ጋር ሌሊት 10 ሰዓት ላይ ትጫወታለች፡፡

በ2022ቱ የኳታር ዓለም ዋንጫ እስከ ግማሽ ፍጻሜ መጓዝ የቻለችው ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ በዚህ ዓለም ዋንጫስ ምን ያህል ርቀት ትጓዛለች የሚለው ይጠበቃል፡፡

ትናንት በተጀመረው የ32ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር አዘጋጇ ሀገር ካናዳ ደቡብ አፍሪካን በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈች ሲሆን፥ በ16ቱ የጥሎ ማፍ መርሐ ግብር ከኔዘርላንድስ እና ሞሮኮ አሸናፊ ጋር ትገናኛለች፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.