የማር የጤና በረከቶች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ማር በርካታ ጠቀሜታ ያላቸውን ንጥረ ነገሮችና ኢንዛየሞችን የሚይዝና ለጤና እና ለመድሃኒትነት የሚያገለግል የምግብ አይነት ነው፡፡
ማር በሚቀነባበርበት ወቅት በሚደረገው ሂደት በተፈጥሮ ያለውን ፀረ – ባክቴሪያነቱንና መርዛማ ነገሮች የመከላከል ባህሪው ሊያጣ ይችላል፡፡
የስነ ምግብ እና የህክምና ባለሙያዎች የተፈጥሮ ማር በርካታ የጤና ጠቀሜታዎች እንዳሉት ይገልጻሉ።
በዋናነትም፦
• ፀረ ባክቴሪያ እና ፀረ ፈንገስ
• ቁስልን ለማከምና ለማዳን
• የምግብ መፈጨት ሂደትን ለማሻሻል
• የጉሮሮ ላይ ህመምን ለመቀነስ
• ጉንፋን እና ደረቅ ሳልን ለማስታገስ
• በሽታ የመከላከል አቅምን ለመጨመር
• የሰውነት ክብደትን ለመቀነስ
• ሃይል ለማግኘት
• ለቆዳ ልስላሴ እና ጥራት
• የሰውነት መቆጣትንና መርዛማነትን ለመከላከል
ማርን ብቻውን ጠዋት ጠዋት በባዶ ሆድ በመጠኑ መውሰድ እንዲሁም ለብ ባለ ውሀ ውስጥ ከሎሚ ጋር በመጨመር መውሰድ ከፍተኛ የጤና ጠቀሜታ እንዳለው ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ይህን ማድረጉ በሰውነት ውስጥ የሚገኝ ቆሻሻን እና ቅባትን ለማስወገድ ይረዳል፡፡
ማርን ከቀረፋ ጋር በመቀላቀል መጠቀምም በሰውነት ውስጥ የሚገኝን የኮሌስትሮል መጠን በ10 በመቶ ለመቀነስ ያግዛል።
ከዚህ ባለፈም ለልብ በሽታ የመጋለጥ እድልን በእጅጉ እንደሚቀንስም የሄልዝ ላይን መረጃ ያመላክታል።