በማሊ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት 29 ወታደሮች ተገደሉ
አዲስ አበባ፣መጋቢት 11፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) በማሊ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት 29 ወታደሮች ተገደሉ።
ጥቃቱ የተፈጸመው በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል ታርኪንት በሚገኘው የጦሩ ካምፕ ላይ መሆኑን መንግስት ገልጿል።
በጥቃቱ ከሞቱት በተጨማሪ ሌሎች አምስት ወታደሮች መቁሰላቸው ተነግሯል።
ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የሚነገርላቸው ታጣቂዎቹ በሰሀራ አካባቢ ባሉ ሀገራት ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት እያደረሱ እንደሚገኙ ተመላክቷል።
ይህን ተከትሎም ፈረንሣይ በአካባቢው ያለውን የሽብር ጥቃት ለመግታት ባለፈው ወር ባካሄደችው ዘመቻ በርካታ ታጣቂዎች መገደላቸው ተገልጿል፡፡
ከዚህ ባለፈም ታጣቂ ቡድኑ ማሊ የሚገኘው ጠንካራ ምሽጉን ጨምሮ ሰፋ ያለ የሰሃራ አካባቢን ማጣቱ ነው የተገለፀው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወታደራዊ ካምፖችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች በመጨመራቸው በማሊ ከፍተኛ ቁጣ መፍጠሩም ነው የሚነገረው።
ባለፈው ጥር ወር በማዕከላዊ ሴጉዩ ወታደራዊ ካምፕ ላይ በሞተር ብስክሌቶች በተፈጸመ ጥቃት 20 ወታደሮች መገደላቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ምንጭ፦ ቢ.ቢ.ሲ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision