በቬንዙዌላ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የ164 ሰዎች ሕይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቬንዙዌላ ትናንት ምሽት በተከታታይ በተከሰተ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የሟቾች ቁጥር 164 መድረሱን የሀገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ዴልሲ ሮድሪጌዝ አስታውቀዋል፡፡
በዋና ከተማዋ ካራካስ በአንድ ደቂቃ ልዩነት የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 2 እና 7 ነጥብ 5 መመዝገቡን የአሜሪካ የጂኦሎጂ ጥናት ተቋም መረጃ አመልክቷል፡፡
አደጋው በ125 ዓመታት ውስጥ ከተከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጥ መጠን ከፍ ያለ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ እስካሁን ቢያንስ የ164 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡
ከሟቾች በተጨማሪ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የተገለጸ ሲሆን፥ በህንጻዎች ፍርስራሽ ስር የሚገኙ ዜጎችን የማፈላለግ የነፍስ አድን ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ላ ጓይራ በተሰኘው የሀገሪቱ ግዛት በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ እስካሁን ማወቅ አልተቻለም፡፡
ከአደጋው አስከፊነት አንጻር የሟቾች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር እንደሚችል የጥናት ተቋሙን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡