የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሮና ቫይረስ ስጋት በምርጫ ኦፕሬሽን ላይ ስለሚኖረው ተጽእኖ ከፖለቲካ ፓርዎች ጋር ተወያየ
አዲስ አበባ፣መጋቢት 11፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አለም አቀፍ ችግር የሆነው የኮሮና ቫይረስ ስጋት በምርጫ ኦፕሬሽን ላይ ስለሚኖረው ተጽእኖ እንዲሁም ሊወሰዱ ስለሚችሉ አማራጭ እርምጃዎች ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ማድረጉን አስታወቀ።
በሁለት የተለያዩ ዙሮች ባካሄዳቸው ውይይቶች ላይ የገዢው ፓርቲን ጨምሮ 45 የፖለቲካ ፓርቲዎች መሳተፋቸው ታውቋል።
በአሁኑ ወቅት ያለው አገራዊ እና አለም አቀፋዊ ሁኔታ ለጥቂት ሳምንታት ከቀጠለ በቀጣይ በዋናነት መፈጸም በሚገባቸው የመራጮች ትምህርት፣ የአስፈጻሚዎች ስልጠና፣ የቁሳቁስ ስርጭት ከፍተኛ የሰው ዝውውርን የሚያሳትፉ በመሆናቸው የመራጮች ምዝገባ ዝግጅት ላይ የሚያደርሰውን ተጽእኖ ላይ ውይይት መደረጉ ተገልጿል።
ወረርሽኙ በዚሁ መልኩ ከቀጠለ÷ ምርጫው ዝርዝር አፈጻጸም እና የጊዜ ሰሌዳ ላይ ሊያደርስ የሚችለው ተጽእኖዎችን እና ሊፈጠሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ግምገማ ከፓርቲዎች እና ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በተከታታይ እንደሚያደርግ አሳውቋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው÷ ይህንን አገራዊ እና አለም አቀፍዊ ችግር በምርጫ ሂደት ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተጽእኖ እንደሚገነዘቡ ገልጸዋል።
አያይዘውም መደረግ አለባቸው ያሏቸውን ሀሳቦች ያጋሩ ሲሆን፥ ከሁኔታዎች በፍጥነት ተለዋዋጭነት አንጻርም ቦርዱ እነዚህን ሁኔታዎች እያገናዘበ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ውይይት እያደረገባቸው ውሳኔዎችን እየወሰነ መሄድ እንዳለበትም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ቦርዱም የዛሬው አይነት ተከታታይ ውይይቶችን እንደሚያከናውን ማስታወቁን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።