Fana: At a Speed of Life!

በራደ ጉልበት ከዘራ ተደግፎ ክላሽ ማንገብ የዳዳው ህገ ወጥ

የህገ ወጡ የሕወኃት አዛውንት መሪዎች የሙጥኝ ያሉት የጥፋት መንገድ፣ የትግራይን ሕዝብ ለከፍተኛ መከራና የሰላም እጦት ዳርጎታል።

አዛውንቱና ህገ ወጡ የሕወሓት ቡድን ንስሃ ከመግባትና ካለፈው ጥፋቱ ከመማር ይልቅ፣ አሁንም ከቀድሞ የእድሜ አቻውና ከአለቃው ሻዕቢያ ጋር በማበር ያረጀውን የግብፅ ተላላኪነት የጦርነት ከበሮ እየደለቀ ይገኛል፡፡

በህገ ወጡ ቡድን ቀስቃሽነት በተፈጠረው የሰሜኑ ጦርነት ኢትዮጵያ ያጣችው የሰው ሕይወትና የወደመው ንብረት የትኛውንም ሰብዓዊ ፍጡር በጥልቅ የሚያሳዝንና የሚያስቆጭ ታሪካዊ ጠባሳ ነው።

ከዚህ ታላቅ ሰብዓዊ ቀውስ በኋላ፣ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የተገኘው ሰላም ለሕዝቡ ትልቅ ተስፋን ፈንጥቆ ነበር።

ይሁን እንጂ በህገ ወጡ ሕወኃት የፖለቲካ ማማ ላይ የተቀመጡት አዛውንት መሪዎች፣ በፈጠሩት ጥፋት ተጸጽተው ንስሃ በመግባትና የሰላምን መንገድ በመከተል ፈንታ፣ አሁንም በውስጣቸው የተሸከሙትን የክፋትና የሴራ ፖለቲካ ይፋ እያደረጉ ይገኛሉ።

በሕዝብ ስቃይ ላይ ሥልጣናቸውን ለማስረዘም የሚጠቀሙባቸው የክፋት ባህርያት የክልሉን ዘላቂ ሰላም አሁንም አደጋ ላይ ጥለውታል።

ግለሰቦቹ የትግራይን ሕዝብ ለከፍተኛ ማኅበራዊ ቀውስ እየዳረጉ፣ ያለውን ውስን ሀብት ለጦርነት ዝግጅትና ለታጣቂዎች ስምሪት ያውሉታል።

ራሳቸው የፈጠሩትን የሕዝብ ስቃይም የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት ለመሳብና የራሳቸውን ሥልጣን ለማስጠበቂያነት ይጠቀሙበታል።

ካለፈው ጦርነት ሰፊ ዕልቂት ተምረው ወጣቶችን ወደ ትምህርትና ልማት መመለስ ሲገባቸው፣ አሁንም ታዳጊዎችንና ወጣቶችን በግዳጅ ወደ ውትድርና በማስገባት ለዳግም ዕልቂት ያዘጋጃሉ።

ይህ የትውልድ ማጥፋት እኩይ ተግባር ትልቁ የክፋት መገለጫቸው ነው።

እነዚህ ህገ ወጦች የተፈጠሩትና ያደጉት በጦርነት አውድ ውስጥ በመሆኑ፣ ሰላማዊ የፖለቲካ ውይይትንና ዲሞክራሲያዊ አሰራርን እንደ ድክመት ይቆጥሩታል።

ከጦርነት ውጪ መኖር ስለማይችሉ፣ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ የጦርነት ከበሮ መደለቃቸውን መርጠዋል።

የራሳቸውን የሥልጣን ዕድሜ ለማራዘም ሲሉ በቡድኑ ውስጥ ለውጥና ሰላም የሚፈልጉ ወገኖችን በማግለል፣ በሕዝቡ መካከል የጥርጣሬና የጥላቻ መርዝ ይረጫሉ።

የውስጥ አንድነት እንዳይኖር በማድረግ ሁልጊዜም ሕዝቡ በስጋት ውስጥ እንዲኖር ይፈልጋሉ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቡድኑን ሕጋዊ ሰውነት በሕግ አግባብ ቢሰርዝም፣ እነዚህ አዛውንቶች በአለቃቸው ሻዕቢያ  ላኪነት ጊዜያዊ አስተዳደሩን በማፍረስ፣ የክልሉን ሃብት እየመዘበሩና ወጣቱን በማፈስ ወደ ታጣቂዎች ካምፕ እያጋዙት ይገኛሉ፡፡

የህገ ወጡ ሕወኃት አዛውንት መሪዎች ያሳዩትና አሁንም እየደገሙት ያለው የክፋት ባህርይ፣ የራስን ሥልጣንና ጥቅም ለማስከበር ሲባል መላውን ትውልድ ለጦርነት እሳት አሳልፎ የመስጠት አባዜ ነው።

ስጋት የማይሆኑበት እድሜ ላይ ቢሆኑም ኢትዮጵያ ወደ አስተማማኝ ሰላምና ብልጽግና መሻገር የምትችለው ከእንደ እነዚህ አይነት የጦርነት ናፋቂዎች እስከ መጨረሻው መቆራረጥ ስትችል ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.