በጠ/ሚ ዐቢይ-ጃክ ማ ኢኒሼቲቭ በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተዘጋጁት የህክምና ቁሳቁሶች ወደ ተለያዩ ሀገራት ተላኩ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ቻይናዊው ባለሃብት ጃክ ማ በጋራ በወሰዱት ኢኒሼቲቭ አማካኝነት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በአፍሪካ ለመከላከል የሚያግዙ የሕክምና መርጃ ቁሳቁሶች ሁለተኛ ዙር ድጋፍ ዛሬ ጠዋት ወደ ዘጠኝ ሀገራት ተልከዋል።
የህክምና ግብዓቶቹ የተላኩላቸው ሀገራትም ደቡብ አፍሪካ፣ ብሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ቶጎ፣ ዛምቢያ፣ ዝምባብዌ፣ ኬኒያ፣ ናይጄሪያ እና ደቡብ ሱዳን መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ-ጃክ ማ ኢኒሼቲቭ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በአፍሪካ ለመከላከል የተዘጋጀው የሕክምና መርጃ ቁሳቁስ የመጀመሪያ ዙር ድጋፍ በትናንትናው ዕለት ሱዳን ካርቱም መግባቱ ይታወሳል።
የሕክምና መገልገያ ድጋፉን የያዘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እቃ ጫኝ አውሮፕላን በካርቱም አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ በሱዳን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ ለሱዳን የጤና ሚኒስትር ዶክተር አክራም አቶም የሕክምና መገልገያዎቹን አስረክበዋል።
ሚኒስትሩ በርክክቡ ወቅት ቫይረሱን ለመከላከል ከፍተኛ ርብርብ በሚጠይቅበት በዚህ ወሳኝ ሰዓት ሱዳን የድጋፉ የመጀመሪያ መዳረሻ በመሆኗ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ በተደረገው ድጋፍ ለኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ እንዲሁም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በሱዳን መንግስትና ሕዝብ ስም የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።
አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ በበኩላቸው ይህ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የተወሰደው ኢኒሺዬቲቭ የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ ወንድም ለሆነው የሱዳን ሕዝብና ለሌሎች የአፍሪካ ሕዝቦች አንገብጋቢ ጉዳዮች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እና መፍትሔ በማፈላለግ ረገድ ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋገጥችበት አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።
ለሱዳን የተደረገው የሕክምና መገልገያዎች ድጋፍ የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ኪቶች፣ የአፍ መሸፈኛ ጭምብሎች እና የሕክምና ባለሙያዎች ከቫይረሱ ጋር ንክኪ እንዳይኖራቸው የሚከላከሉ ልብሶችን ያካተተ ነው።