የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በግብፅ ሻርም አል ሼክ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢሲ) በአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ትኩረቱን የሚያደርገው 27ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በግብፅ ሻርም አል ሼክ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ በሚካሄደው ጉባኤ የአፍሪካ ሀገራት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ለመላመድ እና የታዳሽ ሀይልን መጠቀም ስለሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ኤጀንሲ ባወጣው መረጃ መሰረት በአፍሪካ 116 ሚሊየን ሰዎች ከባህር ወለል ከፍታ በላይ የሚገኙ ናቸው፡፡
በመሆኑም በፈረንጆቹ 2050 የአፍሪካ ሀገራት ከአየር ንብረት ጋር የተያያዙ ተጽእኖዎች ለመግታት በየዓመቱ 50 ቢሊየን ዶላር ፈሰስ ማድረግ እንደሚኖርባቸው የመንግስታቱ ድርጅት አስታውቋል፡፡
በጉባዔው በአጠቃላይ ከ40 ሺህ በላይ ሰዎች የሚሳተፉ ሲሆን ፥ 121 የሀገራት መሪዎች በዚሁ ጉባኤ ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ልዑካቸው ይህንኑ የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ለመታደም ከደቂቃዎች በፊት ግብፅ፣ ሻርም አል-ሼይክ መግባታቸው የሚታወስ ነው።