Fana: At a Speed of Life!

በሪያል ማድሪድ ደጋፊዎች እንዲለቅ የተፈለገው ምባፔ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፈረንሳዊው የፊት መስመር ተጫዋች ኪሊያን ምባፔ ሪያል ማድሪድን እንዲለቅ በርካታ የክለቡ ደጋፊዎች ፊርማ እያሰባሰቡ ይገኛሉ፡፡

ምባፔ የሀገሩን ክለብ ፒኤስጂን በመልቀቅ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ ፍለጋ ሪያል ማድሪድን ቢቀላቀለም በክለቡ በቆየባቸው ሁለት ዓመታት ይህንን ሕልሙን ማሳካት አልቻለም፡፡

በተቃራኒው ፒኤስጂ ከኪሊያን ምባፔ ጋር በተለያየበት ዓመት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ማሳካቱ ይታወሳል፡፡

ተጫዋቹ ሎስብላንኮዎቹን ሲቀላቀል የሪያል ማድሪድ የፊት መስመር ለየትኛውም ተጋጣሚ አስፈሪ ጥምረት እንደሚሆን በብዙዎች ዘንድ ቅድመ ግምት አግኝቶ ነበር፡፡

ምባፔ ነጭ ለባሶቹን ከተቀላቀለ ወዲህ በግሉ ጥሩ የሚባል ጊዜን ቢያሳልፍም ከክለቡ ነባር ተጫዋቾች ጋር የፈጠረው ጥምረት የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ አልሆነም፡፡

በመጀመሪያ ዓመት የሳንቲያጎ ቤርናባው ቆይታው 31 ግቦችን በማስቆጠር የላሊጋው ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ያጠናቀቀ ሲሆን፥ በዚህ የውድድር ዓመት 24 ግቦችን በማስቆጠር የላሊጋውን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እየመራ ይገኛል፡፡

ተጫዋቹ በርካታ ግቦችን በላሊጋው ቢያስቆጥርም ሪያል ማድሪድ ከመሪው ባርሴሎና በ11 ነጥቦች ርቆ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ በዚህ የውድድር ዓመት በ11 ጨዋታዎች 15 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን፥ ቡድኑ መጓዝ የቻለው ግን እስከ ሩብ ፍጻሜ ብቻ ነው፡፡

ሪያል ማድሪድ ኪሊያን ምባፔ በሌለባቸው 5 ተከታታይ ጨዋታዎች በማሸነፉና እሱ ወደ ሜዳ በተመለሰባቸው ከ6 ጨዋታዎች 1 ብቻ ማሸነፋቸው የተጫዋቹ መኖር ክለባቸውን እየጎዳ እንደሆነ ደጋፊዎች እያነሱ ይገኛል፡፡

ተጫዋቹ በ2024 ማድሪድን ከተቀላቀለ ወዲህ ትልቅ ዋንጫ ሳያነሳ ሁለተኛ የውድድር ዘመኑ ሊጠናቀቅ ተቃርቧል።

ቡድኑ ከዋንጫ መራቁንና እሱ ባለበት ጨዋታ ውጤት እያጣ ነው ብለው የሚያስቡ በርካታ የክለቡ ደጋፊዎች ተጫዋቹ ከክለቡ እንዲለቅ ፊርማ እያሰባሰቡ ይገኛል፡፡

የዘንድሮውን የውድድር ዘመን ጨምሮ ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ግቦችን ቢያስቆጥርም ቡድኑ ከዋንጫ ጋር መገናኘት አልቻለም፡፡

የቡድኑ ችግር እሱ ብቻ እንዳልሆነ የሚያሳዩ በርካታ ክፍተቶች ያሉበት ሪያል ማድሪድ ደጋፊዎቹ ሁሉንም የቡድኑን ድክመት በእሱ ላይ ማድረጋቸው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

ቪኒሺየስ ጁኒየር እና ጁድ ቤሊንግሃም በቀድሞ ብቃታቸው ላይ አለመገኘታቸው እንዲሁም ሮድሪጎን በጉዳት ለረዥም ጊዜ ማጣት ሌላው የቡድኑ ትልቁ ክፍተት ነው፡፡

በተጨማሪም ተከላካይ ክፍሉ ላይ ያሉ ተጫዋቾች በጉዳት ምክንያት በወጥነት ቡድኑን አለማገልገላቸው ከክለቡ ችግሮች በጥቂቱ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

አስቸጋሪ የውድድር ዘመን እያሳለፈ የሚገኘው ሪያል ማድሪድ የአሰልጣኝ ለውጥ ቢያደርግም የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ አልቻለም፡፡

በርካታ የክለቡ ደጋፊዎች ተቃውሟቸውን ኪሊያን ምባፔ ላይ ቢያሰሙም ክለቡ በተጫዋቹ ላይ እምነት እንዳለው ተገልጿል።

በሪያል ማድሪድ መልበሻ ክፍል ውስጥ አለመረጋጋት እንደተፈጠረ በስፋት እየተዘገበ ሲሆን፥ በመጪው እሁድ በሚደረገው ተጠባቂው የኤል ክላሲኮ ጨዋታ ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ተሰግቷል፡፡

ከተጠባቂው ጨዋታ በፊት በማድሪድ ቤት ያለው የቡድን ስሜትና አብሮነት የተቀዛቀዘ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.