የአማራ ክልል የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦ ከምከም ወረዳ ተጀመረ
አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 1 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦ ከምከም ወረዳ ተጀምሯል።
የስንዴ ልማቱ የተጀመረው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለና ሌሎች የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት ነው።
ርዕሰ-መስተዳድሩ እንደገለጹት “በዘንድሮ የበጋ ወራት በስፋት ስንዴን በመስኖ ለማልማት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል”።
በመሆኑም አርሶ አደሩ ውጤታማ በመሆን ራሱን ከድህነት ለማላቀቅ የምርት ማሳደጊያ ግብአቶችንና ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ መጠቀም እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በክልሉ የዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በደቡብ ጎንደር ዞን በይፋ መጀመሩን ገልጸው፣ “በሊሞ ከምከም ወረዳ አርሶ አደሮች በአካባቢያቸው ያለ የወል መሬትን ለልማቱ በማዋላቸው ሊመሰገኑ ይገባል” ብለዋል።
በክልሉ ከሚለማው ስንዴም የተወሰነውን ወደ ውጭ ለመላክ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ርዕስ-መስተዳድሩ ተናግረዋል።
ዕቅዱ እንዲሳካ በየደረጃው ያለው አመራርና አርሶ አደሩ ተቀናጅተው እንዲሠሩም አስገንዝበዋል።
ሊቦ ከምከም ወረዳ በ250 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሥራ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር አልማዝ ጊዜ “በክልሉ በበጋ መስኖ ስንዴ ከሚለማው መሬት በሄክታር በአማካይ ከ36 እስከ 40 ኩንታል ለማግኘት ግብ ተጥሎ እየተሠራ ነው” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!