Fana: At a Speed of Life!

ማምረት ብቻ ሳይሆን የግብርና ምርቶች ማከማቻ መጋዘን ሥርዓት መዘርጋትም ቁልፍ ጉዳይ ነው – ወ/ሮ ፍሬዓለም ሺባባው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርና ምርቶችን ከማምረት ባለፈ የምርቶቹ ማከማቻ መጋዘን ሥርዓት መዘርጋት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍሬዓለም ሺባባው ተናገሩ፡፡

የግብርና ምርቶች ማከማቻ መጋዘን ሥርዓትን ለማደራጀት የምክክር አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው፡፡

ወይዘሮ ፍሬዓለም ሺባባው በዐውደ ጥናቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የሀገራችን የምግብ ምርታማነት እንዲያድግ እና የምግብ ዋስትናችን እንዲረጋገጥ ከምንሠራቸው ዐበይት ተግባራት መካከል ብሔራዊ የግብርና ምርቶች ማከማቻ መጋዘን ስርዓትን ቀርፆ በስትራቴጂ መምራት አንዱ ነው ብለዋል፡፡

ምርታማነት እንዲጨምር የግብርና ምርት ማከማቻ መሠረተ ልማት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው÷ አርሶ አደሩ ያመረተውን የሚያስቀምጥበት ደረጃውን የጠበቀ መጋዘን እንደሚያስልገው ተናግረዋል፡፡

ስለሆነም ማምረት ብቻ ሳይሆን ያመረትነውንም በስርዓት ማስተዳደር ይገባል ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

የደረቅና የቀዝቃዛ መጋዘን ሥርዓትን የማደራጀቱ ሥራ በኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ በግሉ ዘርፍ እና በመንግሥት ደረጃ ይሠራል መባሉን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

በዐውደ ጥናቱ የሚነሱ የመፍትሔ ሐሳቦች ተጨባጭ፣ ስትራቴጂክ፣ ሥርዓት (ሲስተማቲክ) እንደሚሆኑ እና በአጭር፣ በመካከለኛ እንዲሁም በረጅም ጊዜ የሚተገበሩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ዐቢይ ኮሚቴ እና የስትራቴጂ ሰነድና የማስፈጸሚያ ዕቅድ የሚያዘጋጁ የቴክኒክ ኮሚቴዎች እንደሚቋቋሙም ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.