Fana: At a Speed of Life!

የመዲናዋ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ የታገዱ አገልግሎቶችን ከመጀመሩ በፊት በሕትመቶች ላይ ለውጥ ማድረጉን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ የታገዱ አገልግሎቶችን ከመጀመሩ አስቀድሞ በሁሉም ሕትመቶች ላይ የሕትመት ለውጥ ማድረጉን አስታውቋል።
 
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዮናስ ዓለማየሁ እንደገለጹት÷ በከተማ አስተዳደሩ ተቋርጦ የነበረው የነዋሪነት መታወቂያ እድሳት ከመጀመሩ በፊት ኤጀንሲው አስቀድሞ አገልግሎት ሲሰጥበት የነበረው ሕትመት ላይ ለውጥ ተደርጓል፡፡
 
በዚሁ መሰረት የልደት፣ የጋብቻ፣ የፍቺ፣ የጉዲፈቻ እና የሞት እንዲሁም የያላገባ እና የነዋሪነት ማንዋል መታወቂያ ካርዶችን ሰብስቦ ሙሉ ለሙሉ በማስወገድ የይዘት ለውጥ እና ተጨማሪ ምስጢራዊ ማሻሻያዎችን በማካተተ አዲስ ሕትመት ተዘጋጅቶ መካተቱን ጠቁመዋል፡፡
 
ማሻሻያው በሕገ ወጥ መልኩ ከተቋሙ ወጥተው በሐሰተኛ ሰነድ አዘጋጆች እጅ ያሉ ማስረጃዎች ዋጋ እንዳይኖራቸው ለማድረግ ያለመ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
 
በተጨማሪም ጠንካራ የሕትመት ስርጭት እና ቁጥጥር ስርዓት እንዲኖር ለማስቻል አሠራር መዘርጋቱን ጠቁመው÷ ይህንኑ ሥራ የሚመራ የስርጭት እና ኦዲት መዋቅር በአደረጃጀት ክለሳ ከዋና መስርያ ቤት እስከ ወረዳ የተፈጠረለት መሆኑን አንስተዋል።
 
አሁን እየተሠራ ባለው ማሻሻያ ኤጀንሲው ባጠረ ጊዜ ግልፅ እና ወጥ የሆነ አሠራር ዘርግቶ እንደሚያጠናቅቅ አቶ ዮናስ አብራርተዋል።
 
በተያዘው ሳምንት ሁሉም ጽሕፈት ቤቶች ኦዲት ተደርገው የተጠናቀቁና ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን የመለየት ሥራ እየተሠራ ነው ማታቸውን የኤጀንሲው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.