ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላት ስትራቴጂካዊ አጋርነት የፖሊሲ ነፃነትን በማክበር መርህ ላይ የተመሰረተ ነው -አምባሳደር ተሾመ ቶጋ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላት ስትራቴጂካዊ አጋርነት የፖሊሲ ነፃነትን በማክበር መርህ ላይ የተመሰረተ ነው ሲሉ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ገለጹ፡፡
የዓለም አቀፍ ልማት ፕሮሞሽን ማዕከል የምረቃ ስነ-ስርዓት ትናንት በቤጂንግ የተከናወነ ሲሆን÷በመርሐ ግብሩ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዩ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል፡፡
በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ የዓለም አቀፍ ልማት ኢኒሼቲቭ ወዳጆችን በመወከል በምረቃ መርሐ ግብሩ ባደረጉት ንግግር÷የፕሮሞሽን ማዕከሉ መመስረት የዓለም አቀፍ ዘላቂ ልማት ግቦች ትግበራን ለማሳለጥ ያግዛል ብለዋል።
የቻይና ዓለም አቀፍ ልማት ትብብር ኤጀንሲ ማዕከሉን በማቋቋም ረገድ ለወሰደው ተጨባጭ እርምጃ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡
ተቋሙ ከተለያዩ ሀገራዊ፣ ክልላዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት የዓለም አቀፍ ዘላቂ ልማት ግቦች፣ የአየር ንብረት ለውጥ ትግበራ፣ የአዲስ አበባ ድርጊት አጀንዳ-ፋይናንስ ለልማት እና የመሳሰሉ ዋና ዋና አጀንዳዎችን አፈፃፀም ለማሻሻልና ለማፋጠን ጉልህ ሚና እንዳለውም አንስተዋል፡፡
አምባሳደር ተሾመ ዓለም አቀፉ ማህበረሰቡ ልክ ቻይና እንዳደረገችው ሁሉ በብሔራዊ የፖሊሲ ማዕቀፍ ውስጥ እጅ ለእጅ ተያይዞ ከሰራ ውጤታማ መሆን እንደሚችልመናገራቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የየሀገራቱን ውስጣዊ ልዩ ሁኔታ ያላገናዘበ ፖሊሲ እንዲሁም የአስተዳደርና የልማት ሞዴሎችን ለመጫን የሚደረግ ሙከራ ፋይዳ የለውም ያሉት አምባሳደሩ፣ ሀገራቱ ልማታዊ አጋሮቻቸውን ጨምሮ ሉዓላዊ የፖሊሲ አማራጮችንና ልማታዊ ሞዴሎችን በነጻነት ሊመርጡና ተግባራዊ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡
ከቻይና ጋር ያለን ስትራቴጂካዊ አጋርነት የፖሊሲ ነፃነትን በማክበር መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን በመጠቆም÷ቻይና ለህዝቦቿ ይጠቅማል የምትለውን የአስተዳደር እና የልማት ሞዴል ምርጫ እናከብራለን ሲሉም በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
