በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ40 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር ተያዘ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ40 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር ተያዘ።
ገንዘቡ የተያዘው ተጠርጣሪዎቹ መነሻውን አዲስ አበባ በማድረግ ወደ ጅግጅጋ ሲጓዝ በነበረ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ውስጥ ገንዘቡን በጫማ ሶል ውስጥ ደብቀው ሊያሳልፉ ሲሞክሩ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ቀርሳ ወረዳ የብሔራዊ መረጃና ደህንነትና የዞኑ ፖሊስ በቅንጅት ባደረጉት ክትትል ነው፡፡
የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ዲቪዥን ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ቶሎሳ ጎሹ፥ ተጠርጣሪዎቹ ከገንዘቡ በተጨማሪ የተለያዩ የባንክ ደብተሮችና የሞባይል ስልኮች ይዘው ነበር ብለዋል።
በዚህም ዶላሩን ደብቀው ሊያሳልፉ የሞከሩ አንድ ወንድና አንዲት ሴትን ጨምሮ አሸከርካሪውና ረዳቱ በቁጥጥር ስር ውለው ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በተሾመ ኃይሉ