በአማራ ክልል የአፈር ማዳበሪያና የምርጥ ዘር እጥረት እንዳይከሰት በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ለመጪው የመኸር ወቅት የምርት ዘመን የግብዓት እጥረት እንዳይከሰት ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
የቢሮው ሃላፊ ሃይለማርያም ከፋለ÷ ለዘንድሮው የመኸር የምርት ዘመን የግብዓት አቅርቦት ስራ በቅድሚያ የተጀመረው ባለፈው ዓመት የገጠመውን እጥረት ታሳቢ በማድረግ ነው ብለዋል።
ለክልሉ 5 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ እንደተፈጸመ የገለጹት ሃላፊው÷ ከ1 ሚሊየን ኩንታል በላይ የሚሆነው ደግሞ ከወደብ ወደክልሉ ደርሶ ለዩኒየኖች መሰራጨቱን ጠቁመዋል።
በአማራ ክልል ለሚመረተው ምርት 400 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር እንደሚያስፈልግ እና እስካሁን 300 ሺህ ኩንታል ዘር መሰብሰቡን ጠቅሰዋል፡፡
ቀሪውን ግብዓት በቅርቡ ለማሟላት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
በክልሉ ለሚመጣው የመኸር ወቅት የግብዓት ችግር እንዳይከሰት በትኩረት እና በትብብር እንደሚሰራም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በኤልያስ አንሙት