የጋምቤላ ክልል አልሚዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራ ገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያየ የኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የጋምቤላ ክልል መንግስት ገለጸ፡፡
የክልሉን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማነቃቃትና የዘርፉን ማነቆዎች ለመፍታት ያለመው ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።
በተሰማሩበት ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የጸጥታ፣ የነዳጅ አቅርቦት፣ የገበያ ትስስር እና ሌሎች ችግሮች እንዲቀረፉላቸው ባለሃብቶች መጠየቃቸውን የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት መረጃ ያመላክታል፡፡
የጋምቤላ ክልል የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሎው ኡቡፕ (ዶ/ር)÷ ከ15 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ከ900 በላይ ነባርና አዲስ ባለሃብቶች በተለያየ የኢንቨስትመንት ዘርፍ መሠማራታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመትም ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 228 አልሚዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል ብለዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት እና የክልሉን ዕድገት ለማፋጠን የባለሀብቶች ተሳትፎ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
በክልሉ መዋዕለ ነዋያቸውን ያፈሰሱ ባለሀብቶችን ውጤታማ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል፡፡
ኢንቨስትመንትን ውጤታማ ለማድረግም በመንግሥት፣ በባለሀብቱና በሕብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለይቶ መፍታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡