በጋምቤላ ክልል ከተፈጸመ የንጹሃን ግድያ ጋር ተያይዞ በተጠረጠሩ የቀድሞ የፖሊስ ኮሚሽነሮችና የልዩ ኃይል አዛዦች ላይ ክስ የመመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ተፈጽሟል ከተባለ የንፁሃን ግድያ ጋር ተያይዞ የተጠረጠሩ የጋምቤላ ክልል የቀድሞ የፖሊስ ኮሚሽነሮችና የልዩ ኃይል አዛዦች ላይ ክስ የመመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ።
ክስ መመስረቻ ጊዜውን የፈቀደው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።
የ15 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ የተፈቀደባቸው ተጠርጣሪዎች የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የቀድሞ ዋና ኮሚሽነር አቡላ ኦባንግ፣ የቀድሞ ም/ኮሚሽነር ቱት ኮር፣ የክልሉ ልዩ ኃይል የቀድሞ ዋና አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ኮንግ ሬክ እና የክልሉ ልዩ ኃይል የቀድሞ ምክትል አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ኡጅዲ ባሬን ጨምሮበአጠቃላይ 12 ናቸው።
በሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም የሸኔ ሽብር ቡድን እና የጋምቤላ ነጻ አውጪ ፓርቲ በጋራ በጋምቤላ ከተማ ባደረሱት ድንገተኛ ጥቃት መነሻ በማድረግ የፀጥታ ኃይሎች የሽብር ቡድኑ ወደ መጣበት ከመለሱት በኋላ፣ በከተማው የሚኖሩ ንጹሃንን በማንነት በመለየት÷ ”ለሽብር ቡድኑ መረጃ ሰጥታችኋል” እንዲሁም ”ጥቃት እንዲደርስ አድርጋችኋል” በሚሉ ምክንያቶች በፖሊስ ኮሚሽኑ ካምፕ አካባቢ በንጹሃን ላይ ከተፈጸመ አሰቃቂ የግድያ ወንጀል ጋር ተያይዞ ተጠርጥረው ምርመራ ሲካሄድባቸው ነበር።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ዘርፍ መርማሪ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ሲያካሂድ የቆየውን ምርመራ በሠነድና በሰው ማስረጃ አጠናክሮ በማጠናቀቅ መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ ማስረከቡን በዛሬው ቀጠሮ ለችሎቱ አብራርቷል።
ዐቃቤ ሕግ ከፖሊስ የምርመራ መዝገቡን መረከቡን ጠቅሶ ከወንጀሉ ውስብስብነት አንጻር ማስረጃዎችን ተመልክቶ ክስ ለመመስረት እንዲያስችለው የ15 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ እንዲሰጠው ጊዜ ቀጠሮ ችሎትን ጠይቋል።
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በበኩላቸው ÷ ዐቃቤ ሕግ እና ፖሊስ ምርመራውን በጋራ እንደሚያካሂዱ ገልጸው ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል።
የዋስትና መብታቸው እንዲፈቀድም ጠይቀዋል።
ጉዳዩን የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎት የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው ውድቅ አድርጓል፡፡
ከወንጀሉ ውስብስብነት አንጻርም ክስ ለመመስረት የክስ መመስረቻ ጊዜ እንደሚያስፈልግ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለዐቃቤ ሕግ የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ ፈቅዷል።
ውጤቱን ለመጠባበቅም ለግንቦት 3 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በታሪክ አዱኛ
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!