Fana: At a Speed of Life!

በ805 ነጥብ 3 ሚሊየን ችግኞች የተጻፈው ዐሻራ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አማካኝነት የደን ሀብቷን ለማሳደግ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን የመቋቋም ጉዞ ዛሬ ላይ የሀገሪቱን ገጽታ ከመቀየር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጠቀስ አርአያነት ያለው ተግባር ሆኗል።

ይህ በየዓመቱ በከፍተኛ ህዝባዊ ንቅናቄ የሚታወቀው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተፈጥሮ ሚዛንን በመጠበቅ የወደፊት ትውልድ ተስፋን በጽኑ መሠረት ላይ የሚያንጽ ብሔራዊ ንቅናቄ ነው።

በየዓመቱ በሚካሄደው መርሐ ግብር በአንድ ጀምበር ብቻ ታሪክ የሚጻፍበት ዕለት አለ። የዘንድሮው በዛሬው ዕለት ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም እንደተለመደው ታሪክ ተጽፎበታል።

በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ መላው ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍ እንደተለመደው ታሪክ ተጽፏል።

በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ሚሊየኖች ከዳር እስከ ዳር በዝናብና በብርድ ሳይበገሩ በመዝመት ምድርን የሚያለመልሙበት ዐሻራቸውን አኑረዋል።

ከማለዳው 12 ሰዓት በጀመረው ንቅናቄ 26 ነጥብ 2 ሚሊየን ሰዎች አሻራቸውን በማኖር 805 ነጥብ 3 ሚሊየን ችግኝ በመትከል የተለመደውን ድል ደግመዋል።

ይህ ታላቅ ድል የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባሻገር፣ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል፣ የውሃ አካላትን ለማበልጸግና የግብርና ምርታማነትን በዘላቂነት ለማሳደግ የጎላ ሚና ይጫወታል።

ከዚሁ ጎን ለጎን፣ የሚተከሉት ችግኞች የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ የፍራፍሬ ተክሎች እንዲሁም የኢኮኖሚ ጥቅም የሚሰጡ የዛፍ ዝርያዎችን ያካተቱ በመሆናቸው ለሀገራችን የኢኮኖሚ እድገት አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።

ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የችግኝ ተከላ ዘመቻዎች ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ የሀገራዊ አንድነት መገለጫ እንዲሆን አድርገውታል።

በከተማም ሆነ በገጠር የሚኖሩ ወጣቶች፣ አባቶች፣ እናቶችና ህፃናት እጅ ለእጅ ተያይዘው ወደ መስክ በመውጣት የራሳቸውን ታሪካዊ ዐሻራ ጽፈዋል።

በአንድ ጀምበር ችግኝ የመትከል ዘመቻ የቁጥር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የጽናት፣ የህብረትና የልማት ታላቅ መገለጫ ሆኗል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.