Fana: At a Speed of Life!

አቶ ሽመልስ አብዲሳ በግርማ የሺጥላ ግድያ የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በአማራ ክልል ብልጽግና ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት ግርማ የሺጥላ ህልፈት የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል፡፡

አቶ ሽመልስ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት የሃዘን መግለጫ÷ አክራሪ ኃይሎች ታታሪና ጀግና የህዝብ አገልጋይ የነበረው ወንድማችን አቶ ግርማ የሺጥላን ነፍስ ዛሬ ነጥቀዋል ብለዋል።

ለሐሳብ ልዕእልና በሐሳብ ሲታገል የነበረውን፣ በመሳሪያ ቃታ መግደል የነዚህን ክሹፍ ኃይሎች መሸነፍ የሚያረጋግጥ ይሆናል እንጂ፤ የህግ የበላይነት የተረጋገጠባት እና ሀሳብ የሚከበርባት ሀገር ከመመስራት ለአፍታም ቢሆን የሚያቆመን አይሆንም ሲሉም  ገልጸዋል።

አክራሪዎች በዚህ ዘመን ውስጥ በሀሳብ ሳይሆን፣ በአፈሙዝ ለማሸነፍ እንዲሁም በጦርነት ስልጣን ለመያዝ ሊያስቡ ይችላሉ ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷በተጨባጭ ግን የዚህ አይነቱ አስተሳሰብ በዚህ ዘመን አይሰራም ብለዋል።

ወንድማችን የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ፣ ጠንካራ አመራርና በሀሳብ የበላይነት የሚያምን እና ይህን ለማረጋገጥ ሲተጋ እንደነበርም አንስተዋል፡፡

በድንገተኛው የአቶ ግርማ የሺጥላ ህልፈት የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን ስገልጽ፣ በተሰበረ ልብ ነው ብለዋል አቶ ሽመልስ በመግለጫቸው።

አቶ ሽመልስ ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹ፣ ለስራ ባልደረቦቹና የትግል አጋሮቹ እንዲሁም ለመላው ህዝዝ መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.