ኢትዮ ኮደርስ የኢትዮጵያን ወጣቶች ወደ መጪው የቴክኖሎጂ ዘመን እያሸጋገረ ነው
በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የሥራ ገበያ በፍጥነት ወደ ዲጂታል ሥርዓት እየተቀየረ ይገኛል።
ኢትዮጵያም ይህንን የቴክኖሎጂ ሽግግር ተከትላ ዜጎቿን በዕውቀትና በክህሎት ለማብቃት ሰፊ ርምጃዎችን እየወሰደች ነው።
በዚህ ረገድ እጅግ ስኬታማና ትልቅ ተፅዕኖ እየፈጠረ ያለው መርሐ ግብር የ5 ሚሊየን የኢትዮ ኮደርስ ብሔራዊ የቴክኖሎጂ ንቅናቄ ነው።
እዚህ ታላቅ ፕሮጀክት ላይ የመደመር መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።
ዓላማውም 5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በመሠረታዊ የኮዲንግ እና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎቶች ማሰልጠን ነው።
ፕሮግራሙ በተለይም ወጣቶችና ሴቶች ባሉበት ቦታ ሆነው በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በር ከፍቷል።
የሥልጠናው ዘርፎችና ይዘት፡-
የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ካለው የኦንላይን የትምህርት ተቋም ዩዳሲቲ ጋር በመተባበር የሚሰጥ ነው።
ሥልጠናው ከ6 እስከ 8 ሳምንት የሚቆይ ሲሆን፤ በፕሮግራሙም ተማሪዎች አራት ዋና ዋና የቴክኖሎጂ ዘርፎችን በነጻ እንዲማሩ ተመቻችቷል።
እነዚህም የዌብ ፕሮግራሚንግ መሠረታዊያን፣ የአንድሮይድ መተግበሪያ ማልማት፣ የዳታ ሳይንስ መሠረታዊያን እና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊያን ናቸው።
እነዚህን ትምህርቶች በተሳካ ሁኔታ ላጠናቀቁ ሠልጣኞች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለውና በሥራ ገበያ ላይ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው የክህሎት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ይሰጣል።
ኢትዮ ኮደርስ ለግለሰቦች ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ በርካታ ጠቀሜታዎችን ይዟል።
ሰልጣኞች ትምህርቱን ካጠናቀቁ በኋላ በኢንተርኔት አማካኝነት ለተለያዩ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መሥራት ይችላሉ።
ይህም ወጣቶች ባሉበት ሆነው የግል ሥራ እንዲፈጥሩና ለሀገራቸው የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገኙ ይረዳል።
ፕሮግራሙ ለሀገሪቱ የዲጂታል ስትራቴጂ ስኬት እንደ ዋና ሞተር ሆኖ ያገለግላል።የመንግሥትና የግል አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ ለማዘመን የሚያስፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ያመርታል።
ወጣቶቹ ባገኙት የኮዲንግ እውቀት በሀገር ውስጥ ያሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለምሳሌ በግብርና፣ በጤና እና በትምህርት ዘርፍ የሚፈቱ የሞባይል መተግበሪያዎችንና ድረ-ገጾችን እንዲያለሙ ያግዛቸዋል።
ሥልጠናው በኮምፒውተር ወይም በሞባይል ስልክ ኦንላይን በቀላሉ መማር የሚቻል በመሆኑ፣ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ለሚገኙ ወጣቶችና በተለይም ለሴቶች ሰፊ ዕድል ሰጥቷል።
እስካሁን የተመዘገቡ ስኬቶች፡-
የኢትዮ ኮደርስ መርሐ ግብር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እጅግ አስደናቂ ውጤቶችን እያገኘ ይገኛል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ3 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ዜጎች ሥልጠናውን በስኬት አጠናቅቀው ዓለም አቀፍ ሰርተፍኬታቸውን ወስደዋል።
ይህም ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያላትን የአቅም ግንባታ ፍጥነትና የወጣቶቿን ለመማር ያለውን ከፍተኛ ተነሳሽነት ያሳያል።
በአጠቃላይ ኢትዮ ኮደርስ ወጣቱ ትውልድ ከቴክኖሎጂ ሸማችነት ወደ ቴክኖሎጂ ፈጣሪነትና ለውጥ አምጪነት የሚሸጋገርበት ታሪካዊ መድረክ ነው።
ማንኛውም ወጣት ይህንን ነፃና ወሳኝ ዕድል በመጠቀም የወደፊት ህይወቱን ብሩህ ለማድረግና የሀገሩን የዲጂታል ጉዞ ለመደገፍ በይፋዊው ድረ-ገጽ ethiocoders.et (https://ethiocoders.et/) ላይ በመመዝገብ መማር ይችላል።