የኢትዮጵያ የተሳካ የሰላም ሂደት ለሱዳን ትምህርት ይሰጣል -አምባሳደር ጀማል በከር
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፓኪስታን የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ጀማል በከር አብዱላ ሱዳን ወደ ሶስተኛ ሳምንት የገባውን ግጭት ለማስቆም ከኢትዮጵያ የተሳካ የሰላም ሂደት ልትማር እንደሚገባ ገለጹ።
በፓኪስታን የሱዳን ልዩ መልዕክተኛ መቀመጫቸውን በኢስላማባድ ያደረጉ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አባል ሀገራት አምባሳደሮችን በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አምባሳደር ጀማል ግጭቶችን በድርድር መፍታት በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያስችል ብቸኛ መንገድ ነው ብለዋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያን የሰላም ሂደት ለመዘከር በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው ዝግጅት ላይ በሱዳን ያሉ ተፋላሚ ወገኖች ግጭታቸውን እንዲያቆሙ ከኢትዮጵያ የሰላም ሂደት ትምህርት እንዲወስዱ መግለጻቸውን አስታውሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሰሜኑ ጦርነት ምን ያህል ዋጋ እንደከፈለች በመዝገብ ላይ የሰፈረ ጉዳይ መሆኑን ያነሱት አምባሳደሩ÷ ከግጭቱ እንድንወጣ ያደረገን የህዝባችን ቁርጠኝነት እና የመላው አፍሪካ እና የሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች ድጋፍ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ሱዳን ችግሮቿን እንድትፈታ ለመርዳት ፍላጎት እንዳላት የገለፁት አምባሳደሩ “የሱዳን ሰላም ለመላው አፍሪካ ሰላም አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስም ይህን ግጭት በውይይት መቋጨት በጣም አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።
አምባሳደሩ እንዳሉት ኢትዮጵያ በችግር ላይ ያሉ ዜጎችን ከሱዳን በማስወጣት ሂደት ብቻ ሳይሆን ለሱዳን ህዝብም ሰብአዊ ድጋፍ ስትሰጥ መቆየቷንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ፈተና ገጥሟት እንደነበር የጠቆሙት አምባሳደሩ÷ በሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ብቸኛው አማራጭ ሰላማዊ ድርድር መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ሰላም ለማምጣት የተጀመረውን የሰላም ሂደት በተሳካ ሁኔታ መፈጸሙን በማብራራትም ጦርነቱ ዜጎችን ለሞት፣ ለረሃብ፣ ለድህነት እና ለስራ አጥነት ዳረገ እንጂ ማንም ሰው ከዚህ ትርፍ አያገኝም ሲሉም ነው የተናገሩት።
በኢትዮጵያ መንግስት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሀት) መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት የአፍሪካ ህብረት የተጫወተውን ሚናም ማድነቃቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።