Fana: At a Speed of Life!

12 የኮሮናቫይረስ ምርመራ ላቦራቶሪዎች በሳምንቱ ሥራ ጀምረዋል- ዶ/ር ሊያ ታደሰ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ተጨማሪ 12 ላቦራቶሪዎች በዚህ ሳምንት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናገሩ።

ይህን ተከትሎ የላቦራቶሪዎች ቁጥር 20 የደረሰ ሲሆን፤ ተጨማሪ 5 ላቦራቶሪዎችም በቅርቡ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩም ተመልክቷል።

የጤና ሚኒስትሯ ዛሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እየተከተላቸው ካሉ መንገዶች አንዱ የምርመራ አቅምን ማስፋት ነው።

ከዚህ ቀደም በአገሪቱ በአጠቃላይ ስምንት ላቦራቶሪዎች አገልግሎቱን ሲሰጡ እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህ ሳምንት ተጨማሪ 12 ላቦራቶሪዎች ወደ ሥራ በማስገባት ቁጥሩን ወደ 20 ከፍ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

ከእነዚህ ውስጥ በአሁኑ ወቅት 11 ላቦራቶሪዎች በተለያዩ የክልል ከተሞች እንዲሁም ዘጠኝ ለቦራቶሪዎች ደግሞ በአዲስ አበባ አገልግሎቱን እየሰጡ እንደሚገኝም ነው ያብራሩት።

በአዲስ አበባ ከሚገኙ ላቦራቶሪዎች መካከል አንዱ በግል ሆስፒታል እንደሚገኝም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ሁሉም ላቦራቶሪዎች በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡ በቀን 3 ሺህ 985 ናሙናዎችን መመርመር እንደሚችሉ ተናግረው፣ ይህን አቅም ይበልጥ ለማሰደግ ተጨማሪ 5 ላቦራቶሪዎች በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምሩ ጠቁመዋል።

ለላቦራቶሪዎቹ አስፈላጊ ግብዓቶችን በቀጣይ ለማሟላት ከተለያዩ አገራት ጋር ንግግር መጀመሩንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

የኮሮናቫይረስን የሚመረምሩ ላቦራቶሪዎች ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ በጤና ጣቢያዎች ጭምር ከሳንባ በሽታና ሳል ጋር የተያያዙ ምልክቶችን ናሙና ወስዶ መመርመር መጀመሩንም አስረድተዋል።

ለቫይረሱ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የቤት ለቤት ምርመራዎችን በማካሄድ የበሽታውን ደረጃ ለማወቅ የሚከናወነው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉንም ዶክተር ሊያ አውስተዋል።

እንደሚኒስትሯ ገለጻ ሚሊኒየም አዳራሽን ጨምሮ ሌሎች የኮሮናቫይረስ ለይቶ ማከሚያ ተቋማትን የማጠናከሩ ሥራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል።

ህብረተሰቡ በመንግስት የሚሰጡ መመሪያዎችን ተግባራዊ በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሚደረገው ጥረት ላይ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም  ዶክተር ሊያ ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.