Fana: At a Speed of Life!

በሀዋሳ ከተማ የመካንነት ምርመራና ህክምና ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀዋሳ ከተማ የመካንነት ምርመራና ህክምና አገልግሎት መሰጠት ተጀመረ፡፡

አገልግሎቱ የጀመረው በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሆስፒታል እና በሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ትብብር ነው።

በሀገር ደረጃ የመካንነት ህክምና የሚሰጠው በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሆስፒታል ብቻ መሆኑን የገለጹት በሆስፒታሉ የመካንነት እና ስነ-ተዋልዶ ማዕከል ሃላፊ ዶክተር መሰረት አንሳ÷ አገልግሎቱን ለማስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ሆስፒታሉ በአዲስ አበባ ማዕከል ብቻ አገልግሎቱን መስጠቱ ካለው የመካንነት ምርመራ እና ህክምና ፍላጎት አንፃር በቂ እንዳልሆነ አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም ሆስፒታሉ የህክምና ቡድን በማደራጀት እና ከሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በሀዋሳ ከተማ አገልግሎት መጀመሩን ገልጸዋል።

የምርመራ እና ህክምና መጀመሩ የአካባቢው ማህበረሰብ በአቅራቢያው አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ጊዜና ወጪ የሚቀንስ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሀዋሳ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዳይሬክተር ዶክተር ፍፁም ወልደገብርኤል በበኩላቸው÷ መካንነትን በተመለከተ የተሳሳተ አመለካከት እንዳለ ተናግረዋል።

መካንነት በምርመራ እና በህክምና የሚድንበት ሁኔታ እንዳለ ጠቅሰው፤ አገልግሎቱ በሀዋሳ መጀመሩ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ልምድ የሚያገኙበትን ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።

በነፃነት ሰለሞን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.