አቶ አሕመድ ሽዴ በአፍሪካ ልማት ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ለመሳተፍ ግብጽ ገቡ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በ2023ቱ የአፍሪካ ልማት ባንክ የቦርድ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ግብጽ ሻርማ ኤል ሼክ ገብተዋል፡፡
ስብሰባው “የአየር ንብረት ተፅዕኖን ለመከላከል እና አረንጓዴ ዕድገትን በአፍሪካ ለማረጋገጥ የግሉን ዘርፍ ማቀናጀት” በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
መድረኩ ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣዮቹ አራት ቀናት በግብፅ ሻርማ ኤል ሼክ የሚካሄድ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
በዚህም የአየር ንብረት ለውጥ በአኅጉሪቱ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመግታት እና ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ባሉ ተግዳሮቶች እና ዕድሎች ላይ ምክክር እንዲደረግ ይጠበቃል፡፡
አቶ አሕመድ ሽዴ በትናንትናው ዕለት በሻርም ኤል ሼክ በተካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የገዥዎች ስብሰባ መሳተፋቸው ተገልጿል፡፡
ስብሰባው የአፍሪካ ልማት ባንክ አስተዳደር ላይ ሪፎርም ለማካሄድ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች እና በኃይል አማራጮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡