ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተለያዩ መርሐ ግብሮችን በስኬት እየተገበረች ነው – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተለያዩ መርሐ ግብሮችን በስኬት እየተገበረች ትገኛለች አሉ።
የአፍሪካ ሕብረት የሥርዓተ-ምግብ አምባሳደር የሌሶቶ ንጉስ ሌትሲዬ ሣልሳዊ በተገኙበት በአፍሪካ የህፃናት እድገትና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ላይ ያተኮረ ከፍተኛ የመሪዎች ውይይት ላይ ተካሂዷል።
በመድረኩ የተሳተፉት አቶ አደም ፋራህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ የህፃናትን ጤናማ እድገት ለማፋጠን የሰቆጣ ቃል ኪዳንን እየተገበረች ትገኛለች ብለዋል።
በተጨማሪም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሌማት ትሩፋት እና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሮችን በስኬት በመተግበር ላይ መሆኗን ገልጸዋል።
በዚህም በሚሊየን የሚቆጠሩ እናቶችንና ህፃናትን ተጠቃሚ ማድረግ ችለናል ነው ያሉት።
መንግሥት የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦትን በአስተማማኝ ደረጃ ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ሁሉም ባለድርሻዎች ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አስገንዝበው፤ የሀገር በቀል ፋይናንስን በማጠናከር እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችሉ ተግባራትን በመፈፀም ለአፍሪካ ብልፅግና የሰው ኃይል ልማት ላይ በጋራ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።