“የዲጂታል ግብርና የፓናል ውይይት” በሳይንስ ሙዚየም በመካሄድ ላይ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር የግብርናውን ዘርፍ ዲጂታላይዝ ማድረግ እንደሚገባ ታምኖበት እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ።
የግብርናና ሳይንስ አውደ ርዕይ አካል የሆነ የዲጂታል ግብርና የፓናል ውይይት “ዲጂታል ግብርና ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት” በሚል መሪ ሀሳብ በሳይንስ ሙዚየም በመካሄድ ላይ ነው።
በፓናል ውይይቱ ላይ የፌዴራል እና የክልል የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የልማት አጋሮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)÷የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር የግብርናውን ዘርፍ ወደ ዲጂታል ግብርና መቀየር እንደሚገባ ታምኖበት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ግብርናውን ዲጂታላይዝ ለማድረግ ከሚሰሩ ተቋማትና ግለሰቦች ጋር እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴዔታ ሁሪያ አሊ በበኩላቸው÷ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የዲጂታሉን ዘርፍ ለመደገፍም ከኢትዮ ቴሌኮምና ሳፋሪ ኮም በተጨማሪ ሶስተኛ የቴሌኮም ካንፓኒ ወደሀገር ውስጥ እንዲገባ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የአፍሪካን ግብርና ወደ ዲጂታል ለመቀየር ምቹ ሁኔታዎች እየመጡ መሆኑን የገለጹት ደግሞ÷የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ማንደፍኖ ንጉሴ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
በኢትዮጵያም በርካታ እድሎች እየመጡ መሆኑን ጠቅሰው÷ኢንስቲትዩቱ እድሎችን በመጠቀም ግብርናውን በዲጂታል በመደገፍ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እንዲሁም የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለመደገፍ እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡
በታምሩ ከፈለኝ