Fana: At a Speed of Life!

በ10 ወራት ከታክስ ዕዳ ከ40 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከታክስ ዕዳ በ10 ወራት ውስጥ ከ40 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ በ10 ወራት ከታክስ ዕዳ ለመሰብሰብ ከታቀደው 30 ነጥብ 39 ቢሊየን ብር ውስጥ 40 ነጥብ 05 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ዕዳ ዳይሬክተር አቶ ቢራራ ልጥገብ ገልጸዋል፡፡

ይህም አፈፃፀም የእቅዱን 131 ነጥብ 77 በመቶ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

ከታክስ ዕዳ የሚሰበሰበው ገቢ ከዓመት ዓመት እድገት እያሳየ መምጣቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ የተመዘገበው አፈፃፀም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻፀር የ9 ነጥብ 14 ቢሊየን ብር እድገት ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡

ውጤቱ የተገኘው ከፍተኛ እና የቆዩ ዕዳዎችን በልዩ ትኩረት ለመሰብሰብ በመሰራቱ እንደሆነ የገለጹት ዳይሬክተሩ÷ ከተሰበሰበው 40 ነጥብ 05 ቢሊየን ብር ውስጥ 18 ነጥብ 06 ቢሊየን ብር ወይም 45 ነጥብ 1 በመቶ ከአዳዲስ እዳዎች፣ 8 ነጥብ 08 ቢሊየን ብር ውል ገብተው በየወሩ እየከፈሉ ካሉ እንዲሁም 14 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ከቆዩ ዕዳዎች የተሰበሰበ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ከታክስ ዕዳ በበጀት ዓመቱ 37 ነጥብ 93 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ ሲሆን÷ ሊሰበሰቡ የሚገባቸውን ዕዳዎች ወደ ቀጣይ ዓመት እንዳይሻገሩ በተሰራው ስራ በጀት ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት ዕቅዱን ማሳካት መቻሉን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የታክስ ከፋዩን ንብረት መዝግቦ እና አደራጅቶ ለታክስ ዓላማ ሲፈለጉ መረጃውን የሚሰጥ ተቋም እንደ ሀገር አለመኖሩ የታክስ ዕዳ አሰባሰቡን ፈታኝ እና ዕዳ በወቅቱ እንዳይሰበሰብ ማድረጉንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.