የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሕገ ወጥ የወርቅ ንግድ ላይ ቁጥጥሩን ማጠናከር አለበት – ቋሚ ኮሚቴው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሕገ ወጥ የወርቅ ንግድ የተሰማሩ አካላት ላይ ቁጥጥሩን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው በክልሉ በባህላዊ የወርቅ ማምረት ስራ ላይ የተሰማሩ ማህበራትንና የግል አነስተኛ ወርቅ አምራች ድርጅቶችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾች ከባህላዊ የወርቅ አመራረትና ሰራተኞችን በማህበር በማደራጀት ወደ ዘመናዊ አሰራር መሸጋገር አለመቻላቸውን የቋሚ ኮሚቴው አባል መሰረት ሽፈራው ገልጸዋል።
ወርቅ በሕገ-ወጥ መንገድ በጥቁር ገበያ ላይ እየተዘዋወረ በመሆኑ እና ወደ ብሔራዊ ባንክ ባለመግባቱ ኢትዮጵያ ከምርቱ የምታገኘው ገቢ በእጅጉ ማሽቆልቆሉን ተናግረዋል።
የክልሉ ማዕድን ሀብት ቢሮ ኃላፊ ካሚል ሁመድ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ከወርቅ ምርት የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ ሕገ-ወጥ የወርቅ ምርት አዘዋዋሪዎች ፈተና እንደሆኑና ምርቱ በሚፈለገው ደረጃ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባት እንዳልቻለ አስረድተዋል።
ቢሮው ቡድኑ የተመለከታቸውን ክፍተቶች በማረም በወርቅ ዘርፍ የማህበረሰብንና የሀገርን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ መግለጻቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመለከታል።