አሜሪካና ቻይና ግንኙነታቸውን ለማደስ እየመከሩ ነው
አዲስ አበባ፣ሰኔ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)አሜሪካ እና ቻይና ሻክሮ የቆየውን ግንኙነታቸውን ለማደስ እየመከሩ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ለሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት ወደ ቻይና አቅንተው ከቻይና አቻቸው ቺን ጋንግ ጋር በቤጂንግ መገናኘታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ደረጃ የተሠጠው የአሁኑ የብሊንከን እና የባለሥልጣናቱ ይፋዊ የቻይና ጉብኝት ሁለቱ ኃያላን ግንኙነታቸውን እንዲያድሱ ለአምሥት ዓመታት አካባቢ ሲጠበቅ የነበረ ነው ተብሏል።
ሁለቱ ቀዳሚ የዓለማችን የምጣኔ ሐብት መሪዎች ከንግድ እስከ ቴክኖሎጂ እና ቀጣናዊ ደኅንነትን በመሰሉ ጉዳዮች ጤናማ የማይመስሉ ፉክክሮች ውስጥ ገብተው መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
ከጉብኝታቸው በፊት በብሊንከን እና በቻይናው አቻቸው ቺን ጋንግ መካከል የተደረገው የሥልክ ውይይትም በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን ከፍተኛ ውጥረት ያመላከተ ስለመሆኑ ተነግሯል፡፡
የአሁኑ የአሜሪካ ባለሥልጣናት የቻይና ጉብኝት ተካሮ የቆየውን ግንኙነታቸውን ለማለዘብ ከሁለቱም ወገኖች ተሥፋ ተጥሎበታል፡፡
ነገር ግን በትናንትናው ዕለት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ስለጉዳዩ ተጠይቀው ለጋዜጠኞች በሠጡት አስተያየት ÷ የቻይናውን ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ እንደገና ሊያገኟቸው እንደሚፈልጉ እና ልዩነቶቻቸውን በውይይት ለመፍታት አማራጭ ሐሳቦች ይዘው እንደሚያቀርቡ መናገራቸው ከብሊንከን እና ከልዑካኑ ውይይት እምብዛም አመርቂ ውጤት አልተገኘ ይሆናል የሚል ሐሳብ አጭሯል፡፡
ቤጂንግ በሀገር ውስጥ ጉዳዮቿ አሜሪካ ጣልቃ እንዳትገባ ትፈልጋለች ፤ በተለይም በታይዋን ጉዳይ ጣልቃ መግባት ቀይ መስመር እንደማለፍ ነው የምትመለከተው፡፡
በመሆኑም በዚህ ጉዳይ ማረጋገጫዎችን ከአሜሪካ እንደምትፈልግ ነው የተነገረው፡፡
ጆ ባይደን እና ሺጂንፒንግ በኢንዶኔዢያ ባሊ ከተካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት ጉባዔ ጎን ለጎን ተገናኝተው በጉዳዩ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ረጅም ውይይት ማካሄዳቸው እንዲሁም በአንቶኒ ብሊንከን የቻይና ጉብኝት ላይ መሥማማታቸው ይታወሳል፡፡
ሁለቱ መሪዎች በፈረንጆቹ መስከረም ወር ላይ ሕንድ ኒውደልሂ በሚካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት ጉባዔ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡
በኅዳር ወር ደግሞ አሜሪካ የእሲያ-ፓስፊክን የምጣኔ-ሐብት ትብብር ስብሰባ ስለምታዘጋጅ ሺ ጂንፒንግ ወደ ሳን ፍራንሲስኮ እንዲያቀኑ ግብዣ ቀርቦላቸዋል፡፡
ሁለቱ ጉባዔዎች የሁለቱ ሀገራት ኃያላን መሪዎች ለብቻቸው ተገናኝተው እንዲወያዩ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡