Fana: At a Speed of Life!

ኢጋድ ሱዳን በድርጅቱ ሙሉ ተሳትፎዋን ለመቀጠል ያሳለፈችውን ውሳኔ በደስታ ተቀበለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የሱዳን ሪፐብሊክ በድርጅቱ ሙሉ ተሳትፎዋን ለመቀጠል ያሳለፈችውን ውሳኔ በደስታ ይቀበላል አለ።

የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ የሱዳን ወደ ኢጋድ የመመለስ ውሳኔ ለቀጣናዊ አንድነት፣ ትብብር እና የጋራ ርምጃ አዲስ ቁርጠኝነትን ያሳያል።

የኢጋድ መስራች አባል የሆነችው ሱዳን ወደ ድርጅቱ መመለሷ የተቋሙ የጋራ ቀጣናዊ ተግዳሮቶችን የመፍታት ችሎታን እንደሚያሳድግ አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት የኢጋድ ሊቀመንበር የሆኑት የጅቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌህ ላደረጉት ጥረት አመስግነው÷ በውይይት እና የጋራ መግባባትን በመፍጠር በኩል ትልቅ ሚና ተጫውተዋል ብለዋል።

ድርጅቱ ሀገሪቱ አሁን ላይ ለገጠማት ተግዳሮቶች ሰላማዊ መፍትሄዎችን በመደገፍ እና ቀጣናዊ መረጋጋትንና ልማትን ለማሳደግ በቅርበት ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.