በአፍሪካ ከ8 ሚሊየን በላይ ፍልሰተኞች ጥገኝነት እና ዓለም አቀፍ ጥበቃ ይሻሉ – የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ ከ8 ሚሊየን በላይ ፍልሰተኞች ጥገኝነት እና ዓለም አቀፍ ጥበቃ እንደሚፈልጉ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ገለጸ፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የዓለም የስደተኞችን ቀን ዛሬ በአዲስ አበባ በኮሚሽኑ ዋና መስሪያ ቤት እያከበረ ነው።
የዘንድሮውን ቀን የኮሚሽኑ የጤና፣ የሰብአዊ ጉዳዮች እና ማህበራዊ ልማት ክፍል ከተባበሩት መንግስታት የፍልሰተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ነው ያዘጋጁት።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የፍልሰተኞች ችግር ውስብስብ በሆኑ ምክንያቶች በአፍሪካ አህጉር የማያቋርጥ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል ብሏል።
በአፍሪካ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶች እና የፖለቲካ አለመረጋጋት በርካታ አፍሪካውያንን በተለያዩ ሀገራት በግዳጅ እንዲፈናቀሉ አድርጓልም ነው ያለው።
ትናንሽ እና ቀላል የጦር መሳሪያዎችን መጠቀም መስፋፋት፣ ሽብርተኝነት እና የአክራሪነት መስፋፋት ሁኔታውን ይበልጥ እንዳባባሰው ነው የተነገረው፡፡
ይህም ለሰዎች ህይወት መጥፋት፣ ቤትና ንብረት መውደም ምክንያት መሆኑ ተጠቁሟል።
መሰል ችግሮችና የምግብ ዋስትና እጦት መጨመር በተለይም በአፍሪካ ቀንድ፣ በመካከለኛው አፍሪካ እና በመካከለኛውና ምእራብ ሳህል ቀጣና ያለው አነስተኛ የዝናብ መጠን እንዲሁም ከሚስተዋሉ ተደጋጋሚ ግጭቶች ጋር ተደማምሮ ከፍተኛ ተግዳሮት መሆኑንም ነው የገለጸው።
የመርሐ ግብሩ ዋነኛ ዓላማም በአፍሪካ ውስጥ ለፍልሰተኞች ትኩረትን ለመፍጠር ፣ ባለድርሻ አካላትም መሰረታዊ የችግሩን መንስኤ የማጥራት እና የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፖለሲዎችን በመተግበር ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈልጉ ተነሳሽነት ለመፍጠር መሆኑ ተመላክቷል፡፡