Fana: At a Speed of Life!

ብፁዕ ካርዲናል ብርሐነ ኢየሱስ የዓቢይ ጾም መግቢያን አስመልክተው መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስትያን ሊቀጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ብርሐነ ኢየሱስ 2018 ዓ.ም የ2018 ዓ.ም ዓቢይ ጾም መግቢያን በማስመልከት አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ብርሐነ ኢየሱስ በመልዕክታቸው እንኳን ለ2018 ዓ.ም የዓቢይ ጾም በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል።

የጾም ወቅት ከተለመደው ዓለማዊ ውሎ ገለል በማለት የመለወጥን ጉዞ ለማጠናከር ወይም ለመጀመር ቤተክርስቲያን የምትሰጠው የጸጋ ወቅት እንደሆነ አውስተዋል፡፡

በዚህ ቅዱስ ወቅት ራስን በመግዛት፣ በሥነ ምግባር በመጠንከር፣ ህሊናን በማዳመጥና በመመርመር ክርስቲያናዊ መታደስን መለማመድ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

የዓቢይ ጾም የኢየሱስ ክርስቶስን ህማማት፣ ሞትና ትንሳኤውን በጥልቅ ማሰብ እና በመንፈሳዊ ተጋድሎ ራሳን ለማዘጋጀት የተሰጠ የጸጋ ጊዜ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በፈተና በተሞላው ዘመናችን ክርስትናችንን በጸሎት፣ በጾም እና በምጽዋት ለማጠናከር የምንተጋበት ቅዱስ ወቅት ነው ሲሉም አመልክተዋል።

ምዕመኑ በዓቢይ ጾም ወቅት ከራስ ባለፈ፣ ለጎረቤቶች፣ ለተጨነቁ ነፍሶች፣ በሀዘን በስቃይ እና በጦርነት ላሉ ወገኖቻች፣ ለሀገር እና ለመላው ዓለም እንዲጸለይ አደራ ብለዋል።

ጎረቤቶቻችንን ባለማሳዘን፣ ከሀሜት በመቆጠብ፣ ክርስቲያናዊ የፍቅር ሥራን በመሥራት፣ የሰዎችን ሰብዓዊ ክብር በመጠበቅ፣ የእግዚአብሔርን ቃል በማዳመጥ እና በእርሱ መኖር፣ በንስሃ፣ በመስዋዕተ ቅዳሴ በማስቀደስ በእውነተኛ መንፈሳዊ ንቃት እንጹም ሲሉም ነው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.