Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ስነ ምግብ የሚኒስትሮች ኮሚቴ የምስረታ ጉባኤ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የምግብ ስርዓትና ስነ ምግብ የሚኒስትሮች ስትሪንግ ኮሚቴ የመጀመሪያ የምስረታ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡

የሚኒስትሮች ኮሚቴው 14 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ያካተተ ሲሆን÷ በግብርና እና ጤና ሚኒስትሮች ይመራል ተብሏል።

ኮሚቴው የተቋቋመው የኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት ሂደት፣ የምግብ እና የተመጣጠነ ምግብ ስትራቴጂ እና የሰቆጣ ቃልኪዳንን ለማስተባበር፣ ፖሊሲዎችን እና የሕግ ማዕቀፎችን ለመምራት መሆኑ ተገልጿል።

በዛሬው የመክፈቻ ጉባኤም በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የተመጣጠነ የምግብ እጥረትን መፍታት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን በመከላከል ላይ ያተኮረ መሆኑ ተመላክቷል።

በ2012 ዓ.ም የተቀረጸውን የኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት እና ስነ ምግብ ትራንስፎርሜሽን መርሐ-ግብር ለማሳካት 14 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በጋራ እንደሚሰሩ ተጠቁሟል።

በኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት እና ስነ ምግብ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ ቀረጻ ላይ ከ40 ተቋማት የተውጣጡ ከ120 በላይ ባለሙያዎች መሳተፋቸው ነው የተገለጸው።

የምግብ ዋጋ ንረትን ማረጋጋት እና ጤናማ አመጋገብን ማበረታታት እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብቶችን መጠበቅ ሌሎች በአጀንዳው የተካተቱ ጉዳዮች ናቸው መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.