አቶ ደመቀ መኮንን ድሬዳዋ ገቡ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ዛሬ ድሬዳዋ ገብተዋል፡፡
ከአቶ ደመቀ መኮንን ጋር የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ አመራሮች ድሬዳዋ ከተማ ገብተዋል፡፡
ከፍተኛ አመራሮቹ ድሬዳዋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ሀርቢ ቡህ፣ የብልጽግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ኢብራሂም ዩሱፍን ጨምሮ የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ “ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ ሐሳብ የሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ወረዳዎች ያስጀምራሉ።
በዞኑ ጉራዋ እና ጋረ ሙለታ እንዲሁም ሌሎች ወረዳዎች ተገኝተው የዘንድሮውን የ2ኛ ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እንደሚያስጀምሩ ይጠበቃል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል ዛሬ ወደ ድሬዳዋ ያቀናው ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ቡድን÷ ከድሬዳዋ ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ እና የካቢኔ አባላት ጋር በመሠረታዊ የልማት ሥራዎች ላይ ተወያይተዋል።