በሕግ የበላይነት ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)”የሕግ የበላይነትና የመልካም አስተዳደር ግንባታ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በፍትሕ ሚኒስቴር አዘጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው መድረኩ÷ ዓላማ በሕግ የበላይነት፣ በመልካም አስተዳደርና በፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ እንዲሁም በህግ የበላይነት ግንባታ የአስተዳደር ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ሚና ላይ ግንዛቤ ለማሳደግ መሆኑ ተመልክቷል ።
በሀገሪቱ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የፍርድ ቤቶችና የዴሞክራሲ ተቋማት ሚና ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም ይጠበቃል።
በመድረኩ ላይ የፍትህ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እፀገነት መንግስቴና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ተገኝተዋል ።
በተጨማሪም የተለያዩ የፌዴራል እና የክልሎች የፍትሕ አካላትና ተጋባዥ እንግዶች እየተሳተፉ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።