የጅቡቲ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ልዑክ በኢትዮጵያ ጉብኝት ሊያደርግ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጅቡቲ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ጉብኝት ሊያደርግ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በሰጡት መግለጫ ÷112 አባላትን የያዘ የጅቡቲ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ልዑክ ከሰኔ 25 እስከ 30 ቀን 2015 በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደርጋል ብለዋል።
ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ልዑካን ቡድን አባላት ከምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎችን እንዳካተተ አንስተዋል፡፡
ልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ቆይታው የሕዝብ ለሕዝብ ውይይቶችን እና በአረንጓዴ አሻራ ተሳትፎ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
የልዑኩ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ከገጽታ ግንባታ አንጻር በጎ ሚና እንደሚጫወት የገለጹት አምባሳደር መለስ÷በገጽታ ግንባታ እና ኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።