አንድን ግለሰብ በመግደል አስከሬኑን ቆራርጠው መጸዳጃ ቤት ውስጥ የጣሉት ተከሳሾች በሞት እንዲቀጡ ተወሰነ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 678 ሺህ ብር የሚያወጣ በዱቤ የተሸጠን በቆሎ ለግል ጥቅማቸው ለማዋል የንብረቱን ባለቤት በመግደል አስከሬኑን በመቆራረጥ መጸዳጃ ቤት ውስጥ የጣሉት ሁለት ተከሳሾች በሞት እንዲቀጡ ተወሰነ፡፡
ድርጊቱ የተፈጸመው በሀዲያ ዞን ዱና ወረዳ መሆኑን የደቡብ ክልል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
ከተከሳሾቹ አንዱ የንብረቱን ባለቤት በጥይት ከገደለ በኋላ አስከሬኑን ሁለቱም ተከሳሾች ቆራርጠው በማዳበሪያ በመጠቅለል መጸዳጃ ቤት ውስጥ መክተታቸው ተገልጿል፡፡
የወረዳው ፖሊስም ለአራት ቀናት ያህል ባደረገው ፍለጋ÷ አገልግሎት መሥጠት ባቆመ አሮጌ መጸዳጃ ቤት ውስጥ የሟችን የተቆራረጠ አስከሬን ማግኘቱን አስታውቋል።
ወንጀሉን የፈጸሙት በድለላ ሥራ የሚተዳደርና በሟች ግቢ ውስጥ ቤት ተከራይቶ የሚኖር አቶ ፈለቀ በቀለና በጫኝና አውራጅ የቀን ሥራ የሚተዳደር አቶ ሳሙኤል አበራ የተባሉ ግለሰቦች መሆናቸው ተመልክቷል፡፡
በዚህም 1ኛ ተከሳሽ አቶ ፈለቀ በቀለ ከግል ተበዳይ አቶ አባተ ኢቶሬ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም ግምቱ 678 ሺህ ብር የሆነ 230 ኩንታል በቆሎ ተቀብሎ በዱቤ ማሻሻጡም ነው የተገለጸው፡፡
ይህንኑ ገንዘብ ለግል ጥቅሙ ለማዋል በማሰብም በመጠጥ ተገፋፍቶ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 4 ሠዓት እስከ 8 ሠዓት ባለው ጊዜ የግል ተበዳይን ወደ ቤቱ በመጥራት በጥይት መግደሉ ተረጋግጧል፡፡
ከ2ኛ ተከሳሽ አቶ ሳሙኤል አበራ ጋር በመሆንም የሟችን አስከሬን ቆራርጠው በሦስት ማዳበሪያ በማድረግ መጸዳጃ ቤት ውስጥ መክተታቸውን 1ኛ ተከሳሽ አረጋግጧል፡፡
የሀድያ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ሰኔ 22 ቀን 2015 ዓ.ም ባስቻለው የወንጀል ችሎት ሁለቱም ተከሳሾ በሞት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡