Fana: At a Speed of Life!

የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሰላም እንዲጠናቀቅ የጋራ የፀጥታ ዕቅድ ላይ ምክክር ተካሄደ

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሰላም እንዲጠናቀቅ የጋራ የፀጥታ ዕቅድ ላይ ምክክር ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች እና የክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል÷ትውልድ የሚቀረፅበትን የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ተልዕኮ ወስዶ በሃላፊነት መስራት አለበት ብለዋል፡፡

ከሐምሌ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በ102 የፈተና ጣቢያዎች የሚካሄደው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ሀገራዊ የፀጥታ ሁኔታውንና የክረምቱን የአየር ሁኔታ ያገናዘበ በርካታ የሰው ኃይል መመደቡን ጠቁመዋል፡፡

ፈተናው ከሥርቆት በፀዳ መልኩ እንዲካሄድ ሁሉም ኃላፊነቱን ወስዶ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

 

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ም/ ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ÷ በአማራና በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች በፈተና ጣቢያዎች የፀጥታ ችግሮች እንዳይከሰቱ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገልፀዋል።

ተማሪዎች ለፈተና ሲመጡ የሀኪም ማዘዣ የሌለው መድሃኒት በሽሮፕም ሆነ በታብሌት፣ የህክምና መስጫ መርፌ፣ የአንገት ሀብል፣ የፀጉርና የጆሮ ጌጥ፣ ከጋብቻ ቀለበት ውጭ ፈርጥ ያለው የጣት ቀለበት እና የእጅ አንባር አድርጎ መምጣት ክልል መሆኑ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ አይ-ፓድ፣ ታብሌት፣ ላፕቶፕ፣ ስማርት ሰዓት፣ ሲዲ፣ ሚሞሪ፣ ሚሞሪ ሪደርና ኦ-ቲጂ ኮንቨርተር እንዲሁም ፎቶ የሚያነሱ እና ድምፅ የሚቀርፁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ይዞ መገኘት የተከለከለ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡፡

የተከለከሉ መሣሪያዎችን በዩኒቨርሲቲዎቹ ግቢ ውስጥም ሆነ በዙሪያው ይዞ መገኘት፣ ፈተና ከተጀመረ ከ30 ደቂቃ በኋላ ወደ ፈተና ክፍል መግባት እና ፈተናው ተጀምሮ 45 ደቂቃ ሳይሞላ ከፈተና ክፍል መውጣት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲ ግቢ ወስጥ በግልም ሆነ በቡድን ከፍተኛ ድምጽ ማሰማት የተከለከለ ነው ተብሏል፡፡

ይህንን ተላልፎ በተገኘ ተማሪ ላይ ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑንም ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፋንታ ማንደፍሮ(ዶ/ር) ÷ መንግስት የትምህርት ሥርዓቱን ለመቀየር ከፍተኛ በጀት መድቦ ቀላል የማይባሉ ተግባራትን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ የትራንስፖርት ችግሮችን ለመቅረፍ፣ ለተማሪዎች ከትምህርት ቤት ጀምሮ በወረዳና በዞን ትምህርት ቢሮ አማካኝነት የፈተና መመሪያ ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት እንደተደረገ መገለጹን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል።

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.