ኢትዮጵያ የአፍሪካ የሥራ ጉባዔን ልታስተናግድ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመጀመሪያው የአፍሪካ የሥራ ጉባዔ ሊካሄድ መሆኑን የሥራና ክኅሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በአኅጉር አቀፍ ደረጃ ለሦስተኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው ጉባዔ በሥራና ክኅሎት ሚኒስቴር ፣ በአፍሪካ ኅብረትና በአፍሪካ ኤሌክትሮኒክስ ትሬድ አዘጋጅነት ከሠኔ 30 እስከ ሐምሌ 2 ቀን 2015 ዓ.ም ለተከታታይ ሦስት ቀናት ይካሄዳል።
ጉባዔው በአፍሪካ የሥራ ፈጠራን ለማበረታታት እና የሥራ አጥነት ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ያለመ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
በአኅጉሪቱ የሚገኙ ወጣቶችን በቅንጅት እንዲሠሩ እንደሚያስችልም የሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን ተናግረዋል።
በመንግስትና በግሉ ዘርፍ መካከል ትብብርና በመፍጠር በአኅጉሪቱ ያለውን ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር በመለየት ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠትም የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።
በቤተልሔም መኳንንት