Fana: At a Speed of Life!

የዓለም ጤና ድርጅት አስከፊ የአየር ንብረት ለውጥ ሊያጋጥም እንደሚችል አስጠነቀቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ጤና ድርጅት በዓለማችን ላይ አስከፊ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ሊያጋጥም እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም፥ በፈረንጆቹ 2023 አስከፊ የአየር ንብረት ለውጦች ተባብሰው መቀጠላቸውን እና በተያዘው ሳምንት በዓለም ከፍተኛው የሙቀት መጠን መመዝገቡን ገልፀዋል፡፡

የአየር ንብረት ቀውስ በሰዎች ጤና ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ያነሱት ዳይሬክተሩ÷ እየታየ ያለው የአየር ንበረት ለውጥ በዓለማችን ላይ ረሃብ፣ ስደት እና የተለያዩ በሽታዎች ስጋት መደቀኑንም አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም በሚታዩ የአየር ንብረት ለውጦች ምክንያት በሚቀጥሉት ወራት ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ከባድ አውሎ ነፋስን እና ከፍተኛ የሙቀት መጠንን ጨምሮ የተለያዩ ክስተቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ነው ዳይሬክተሩ ያስጠነቀቁት፡፡

አሁን ላይ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው የተራዘመ ድርቅ በቀጠናው ማህበረሰብ የጤና ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ በጂቡቲ፣ ኬንያ፣ሶማሊያ፣ደቡብ ሱዳን እና ኡጋንዳ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከ60 ሚሊየን በላይ ዜጎች ለምግብ ዋስትና ችግር መጋለጣቸውንም አብራርተዋል፡፡

የአሜሪካ ብሔራዊ የአካባቢ ትንበያ ማዕከል ሰኞ እለት ከፍተኛውን የሙቀት መጠን ይፋ ማድረጉን አር ቲ በዘገባው አስታውሷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.