Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ባይደን ለዩክሬን ክላስተር ቦምብ እንዲሰጥ ያሳለፉትን ውሳኔ እንደሚተገብሩት አረጋገጡ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 1 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለዩክሬን ክላስተር ቦምብ እንዲሰጥ ያሳለፉትን ውሳኔ እንደሚተገብሩት አረጋገጡ።

 

ፕሬዚዳንቱ ‘በጣም ከባድ’ ያሉትን ውሳኔ ለማሳለፍና ለመወሰን ጊዜ እንደወሰደባቸውና፥ ዩክሬን ከገጠማት የተተኳሽ እጥረት አንጻር እንደሚተገብሩት አረጋግጠዋል።

 

ባይደን ከሲ ኤን ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ በጉዳዩ ላይ ከአጋር ሀገራት ጋር መነጋገራቸውን ጠቅሰዋል።

 

የፕሬዚዳንቱ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫኒ በሰጡት መግለጫ፥ አሜሪካ ክላስተር ቦምቦች በንጹሃን ላይ ሊያደርሱት የሚችሉትን ጉዳት ግምት ውስጥ በማስገባት ሳትልክ መቆየቷን ገልጸዋል።

 

ይሁን እንጅ ዩክሬን ከገጠማት የጦር መሳሪያ ችግር አንጻር እዚህ ውሳኔ ላይ ተደርሷል ነው ያሉት።

 

ክላስተር ቦምብ በርካታ ትናንሽ ቦምቦችን የሚይዝና ከምድር ወደ ሰማይ የሚተኮስ ሲሆን፥ በወደቀበት አካባቢ ሲፈነዳ እጅግ ከባድ ጉዳት እንደሚያደርስ ይነገራል።

 

ይህ ቦምብ በወደቀበት ስፍራ ሰፊ መጠን ያለውን ስፍራ በመሸፈን የሚፈነጣጠር መሆኑ ደግሞ የጉዳቱን መጠን የከፋ ያደርገዋልም ነው የሚባለው።

 

እነዚህ ቦምቦች በወደቁበት ስፍራ ሳይፈነዱ ለበርካታ ጊዜ እንደሚቆዩም ነው የሚነገረው፤ ይህ ደግሞ በንጹሃን እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ የደህንነት ስጋትን የሚጥል ነው ተብሏል።

 

የክላስተር ቦምብ ከ120 በላይ ሀገራት ጥቅም ላይ እንዳይውል መታገዱን ቢቢሲ አስነብቧል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.