አማራ ክልል የግብርናውን ምርታማነት ለማሳደግ በተደረገው ጥረት አመርቂ ውጤት ተገኝቷል – ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ባለፈው የምርት ዘመን የግብርናውን ምርታማነት ለማሳደግ በተደረገው ጥረት አመርቂ ውጤት መገኘቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ገለጹ።
የክልሉ ካቢኔ አባላት የ2015 ዓ/ም በጀት ዓመት የመንግስት ስራ አፈጻጸምን እና በቀጣይ የክረምት ወራት እቅድ ላይ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ባለፈው በጀት ዓመት በክልሉ በግብርናው ዘርፍ፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በመሰረተ ልማት እንዲሁም በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች እንደነበሩ ተገልጿል።
ርዕሰ መስተዳደሩ ክልሉ በጦርነት እና በጸጥታ ችግር ውስጥ የከረመ ቢሆንም የልማት እቅዶችን ዳር ለማድረስ በተደረገው ርብርብ ተስፋ ሰጪ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
በተጨማሪም÷ ባለፈው የምርት ዘመን የግብርናውን ምርታማነት ለማሳደግ በተደረገው ጥረት አመርቂ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም የኑሮ ውድነትን ለመቀነስና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሰብል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ አንስተዋል።
በቀጣይ የክረምት ወራት የሚከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር፣ የመኸር ሰብል ልማት፣ የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች አገልግሎትና ወቅታዊ ስራዎች በተያዘላቸው እቅድ መሰረት ተፈጻሚ እንዲሆኑ የክልሉ መንግሥት ድጋፍና ክትትሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበትም ማሳሰባቸውን ከክልሉ ርዕሰ መስተደደር ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡