የኦሮሚያ ክልል መንግስት በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ሆኖ የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎችን ሰርቷል- አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል መንግስት በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ሆኖ የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ የልማት ስራዎችን አከናውኗል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት 6ኛ የስራ ዘመን 2ኛ ዓመት 5ኛ መደበኛ ጉባኤ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ÷ ለጨፌው የ2015 በጀት ዓመት የክልሉን የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
በሪፖርታቸውም በበጀት ዓመቱ በክልሉ ለ2 ነጥብ 3 ሚሊየን ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ለወጣቶች የመስሪያ ቦታ ችግርን ለመቅረፍ 67 ሺህ ሄክታት መሬት እና 1 ሺህ 146 ሼዶችን የማመቻቸት ስራ መከናወኑን አንስተዋል፡፡
የወጣቶችን የፋይናንስ ችግርን ለመቅረፍም የ4 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል በበጀት ዓመቱ 8 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እስካሁን 7 ነጥብ 2 ሚሊየኑ በዘር መሸፈኑን አስረድተዋል፡፡
በክልሉ በበልግ ወቅት በተከናወነ እርሻ 7 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኙትንም ነው አቶ ሽመልስ የተናገሩት፡፡
በክልሉ 9 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ ባጋጠመው እጥረት ሳቢያ 5 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል ማስገባት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ውስጥም 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ነው የገለጹት፡፡
ከጸረ ሙስና ጋር ተይይዞ 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር መታገዱን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብሩ ለመንግስት ገቢ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከህብረተሰቡ 1ሺህ 900 በላይ የሙስና ወንጀል ጥቆማዎች ደርሰው 1 ሺህ 431 ጉዳዮች መጣራታቸውን አብራርተዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 78 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 82 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡም ተመላክቷል፡፡