ለጤና ተቋማት መልሶ ግንባታ የሚውል የ31 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ተደረገ
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የአውሮፓ ሕብረት በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል የ31 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አድርጓል፡፡
በአማራ፣ አፋር እና ትግራይ ክልሎች የሚገኙ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን 160 የጤና ተቋማት መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ገንዘብ ነው ሕብረቱ ድጋፍ ያደረገው፡፡
ድጋፉም÷በዋናነት የተጎዱ ጤና ጣቢያዎችን መልሶ ለማቋቋም፣ የፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ወገኖች ማገገሚያ ማዕከላትን ለማጠናከር እንዲሁም አማራጭ የጤና አገልግሎቶች ተደራሽ እንዲሆኑ ለማድረግ ይውላል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም የድጋፍ ፕሮጀክቱ ÷ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለማድረግ እንደሚውል የሕብረቱ መረጃ ያመላክታል፡፡