Fana: At a Speed of Life!

ለዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ከተቀመጡት ተማሪዎች ውስጥ 40 ነጥብ 65 በመቶዎቹ የማለፊያ ነጥብ አስመዘገቡ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 8 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ከተቀመጡት ተማሪዎች ውስጥ 40 ነጥብ 65 በመቶዎቹ የማለፊያ ነጥብ ማስመዝገባቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ ከሰኔ 30 ቀን ጀምሮ ለስድስት ቀናት ሲሰጥ የቆየው የዩኒቨርሲቲ ትምህርት መውጫ ፈተና በስኬት መጠናቀቁን ገልፀዋል።

ለመውጫ ፈተና ሊቀመጡ ይችላሉ ተብሎ ተገምቶ ከነበረው 240 ሺህ ተማሪዎች የመውጫ ፈተናውን 194 ሺህ 239 ተማሪዎች ብቁ ሆነው ለፈተና መመዝገባቸውንም ነው የተናገሩት።

ከዚህ ውስጥ ከ48 የመንግስት ተቋማት 84 ሺህ 627 ተማሪዎች እና ከ171 የግል ተቋማት 109 ሺህ 612 ተማሪዎች የመውጫ ፈተናውን ለመውሰድ መመዝገባቸውም ነው የገለጹት።

የመውጫ ፈተናውን ለመውሰድ ከተመዘገቡት ውስጥ ከመንግስት ተቋማት 77 ሺህ 981 ተማሪዎች እንዲሁም ከግል ተቋማት 72 ሺህ 203 ተማሪዎች በድምሩ 150 ሺህ 184 ተማሪዎች ፈተናውን ወስደዋል ብለዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ 61 ሺህ 54 ተማሪዎች ወይም 40 ነጥብ 65 በመቶ የማለፊያውን ነጥብ አስመዝገበዋል ነው የተባለው፡፡

ለተቋማትም የተማሪዎቻቸውን ውጤት የመላክ ሥራ መጀመሩንም ጠቁመዋል።

በአዲሱ ሙሉነህ

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.